Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ መንግስት ለሚያደርጋቸው ጥረቶች የዩኒሴፍ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል – የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት ትኩረት በሚሰጣቸው መስኮች እና ከድርቁ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ጉዳት ለመቀነስ ለሚያደርጋቸው ጥረቶች የተባበሩት መንግስታት የህፃናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ተናገሩ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ራስል ጋር ድርጅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ እያደረጋቸው ስላሉ የልማት እና የሰብአዊ ድጋፍ ሥራዎች አጠናክሮ መቀጠል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በውይይታቸው አቶ ደመቀ፥ ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በሕፃናት ፣ በትምህርት ፣ ጤና እና የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ስራዎች ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ ያለ የልማት አጋር ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች እንዲሁም በሀገሪቱ የነበረው ጦርነት ብዙ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ማስከተሉን ገልጸዋል፡፡

ይህም በአካባቢዎቹ የሚኖሩ ዜጎች እንደ ትምህርት፣ ጤና እና ንፁህ መጠጥ ውሃን የመሳሰሉ መሰረታዊ አገልግሎቶችን እንዳያገኙ ማድረጉንም ነው ያስረዱት።

በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው ድርቅም በኢትዮጵያ ውስጥ በሰዎች እና እንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ ደመቀ፥ መንግስት አቅሙን አስተባብሮ የጉዳት መጠኑን ለመቀነስ እና አደጋውን ለመከላከል መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በጦርነት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት እና ለድርቅ ተጎጂዎች አስቸዃይ የሰብአዊ እርዳታን ተደራሽ ለማድረግ እንደ ዩኒሴፍ ያሉ የልማት አጋሮች ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን በበኩላቸው÷ መንግስት ትኩረት በሚሰጣቸው መስኮች ላይ ዩኒሴፍ ሁለንተናዊ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጠናው የተከሰተው ድርቅ በሌሎች አለም ክፍሎች ባሉ ግጭቶች ተሸፋፍኖ ትኩረት እንዳያጣ በማሰብ በአፍሪካ ቀንድ ጉብኝት እያደረጉ እንደሚገኙ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሯ፥ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለድርቁ ተገቢ ትኩረት እንዲሰጥ በማድረግ ለተጎጂዎች አፋጣኝ ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ የሚያስችል ሃብት የማሰባሰብ ስራ እንደሚሰራም ገልፀዋል።

በግጭት እና የተፈጥሮ አደጋ ይበልጥ ሕፃናት ተጎጂ መሆናቸውን አስታውሰው ጉዳቱን ለመቀነስ የኢትዮጵያ መንግስት ለሚያደርጋቸው ጥረቶች ዩኒሴፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.