Fana: At a Speed of Life!

በነገው ዕለት በመዲናዋ ከሚካሄደው የኢፍጣር መርሃ ግብር ጋር ተያይዞ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶች ይፋ ተደረጉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በነገው ዕለት በአዲስ አበባ ከሚካሄደው ታላቁ የኢፍጣር መርሃ ግብር ጋር ተያይዞ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶችን የፀጥታና የደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል፡፡

የከተማዋን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ከመላው ሠላም ወዳድ ህዝብ ጋር ሆኖ ተግባሩን በመወጣት ላይ የሚገኘው የፀጥታና የደህንነት ግብረ ኃይል የታላቁን ረመዳን ፆምን አስመልክቶ ለሚደረገው የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሃ ግብር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን አስታውቋል፡፡

ሠላም ወዳዱ ህዝብም ለፀጥታ አካላት የሚያደርገውን ቀና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል የጋራ ግብረ ኃይሉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

በነገው ዕለት ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ጀምሮ መርሃ ግብሩ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከቅዱስ ኡራኤል አካባቢ ጀምሮ እስከ መስቀል አደባባይ እና በዙሪያዋ የሚገኙ መንገዶች ለተሽከርካሪዎች ዝግ እንደሚሆኑም የፀጥታና የደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል፡፡

በዚህም መሰረት÷ ከመገናኛ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ሀያ ሁለት ወይም ዘሪሁን ህንፃ አካባቢ ዝግ ይደረጋል፣ ከወሎ ሰፈር ወደ መስቀል አደባባይ ወሎ ሰፈር ኦሎምፒያ፤ ከጎተራ ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ አሽከርካሪዎች አጎና ሲኒማ፤ ከጦር ኃይሎች በሜክሲኮ ወደ መስቀል አደባባይ እና ከሜኪሲኮ ወደ ብሔራዊ ቴአትር ለሚጓዙ ሜክሲኮ አደባባይ፤ ከጌጃ ሰፈርና ከጎማ ቁጠባ በሰንጋ ተራ ወደ መስቀል አደባባይ ለሚጓዙ የቀድሞው ደሳለኝ ሆቴል መስቀለኛ ላይ፤ ከጎማ ቁጠባ ወደ ብሔራዊ ለሚጓዙ ጎማ ቁጠባ ላይ እና ከሜክሲኮ ወደ ፖስታ ቤት ለሚሄዱ ሚትሮሎጂ አካባቢ እንዲሁም ከጥቁር አንበሳ ሼል ወደ ኢሚግሬሽን ለሚሄዱ አሽከርካሪዎች ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በር አካባቢ፤ከተክለኃይማኖት በጎላ ሚካኤል ለሚመጡ ጎላ ሚካኤል መስቀለኛ ላይ እና ከተክለኃይማኖት ወደ ቴዎድሮስ አደባባይ ለሚመጡ ተክለኃይማኖት ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ከተክለ ኃይማኖት በሶማሌ ተራ ወደ ባንኮ ዲሮማ ለሚመጡ አሽከርካሪዎች ሸዋ ሱፐር ማርኬት ጋር ዝግ የሚደረግ ይሆናል፡፡

እንዲሁም ከቀድሞ አትክልት ተራ አካባቢ በአሮጌው ፖስታ ቤት ወደ ቸርችል ጎዳና የሚወስደው መንገድ አሮጌው ፖስታ ቤት፤ ከደጎል አደባባይ ወደ እሪ በከንቱ ደጎል አደባባይ ላይ እና ከአራት ኪሎ በፓርላማ ወደ ውጭ ጉዳይ የሚወስደው መንገድ ሸራተን ሆቴል መውረጃ ላይ፤ ከአራት ኪሎ በብሔራዊ ቤተ መንግስት ወደ መስቀል አደባባይ ለሚጓዙ አሽከርካሪዎች ብሔራዊ ቤተ መንግስት መስቀለኛ ላይ የሚዘጋ ሲሆን ከካዛንቺስ ሼል ወደ ፍል ውሀና ወደ ባምቢስ የሚወስዱት መንገዶች ካዛንስ ሼል ላይ ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ጀምሮ የኢፍጠር ፕሮግራሙ እስከሚጠናቀቅበት ሰዓት ድረስ ዝግ የሚደረጉ ይሆናል፡፡

በተጨማሪም በተገለፁት መንገዶች ላይ ለአጭርም ሆነ ለረጅመ ሰዓታት ተሽከርካሪዎችን አቁሞ መሄድ የተከለከለ ሲሆን ህብረተሰቡ መርሃ ግብሩ በሠላም ተጀምሮ በሠላም እንዲጠናቀቅና ማንኛውም ዓይነት አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙ በፖሊስ የመረጃ ስልኮች 0111 11 01 11 እና ነፃ የስልክ መስመር 991 ላይ በመደወልና መረጃ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ የፀጥታና የደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.