Fana: At a Speed of Life!

የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ በመሥራት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ወቅታዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረጉ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ በመሥራት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2014ዓ/ም በጀት ዓመት የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ዛሬ ከዋናው መስሪያ ቤት እና ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች ጋር ውይይት አካሂዷል።

በሀገር ውስጥ ፣በቀጣናው ፣በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈጠሩ ሁነቶች ያስከተሉት ተዛማች ተፅዕኖ እና ያ ተፅዕኖ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ የፈጠረውን ጫና ለመቀልበስ፤ በፖለቲካ፣በኢኮኖሚ፣በፐብሊክ እና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የተከወኑ ሥራዎች ያስገኙት ውጤት ፤ የነበሩ ጠንካራ ጎኖች እና በቀጣይ ሊስተካከሉ የሚገባቸውን መሰናክሎች በማጠቃለል ቀርቧል ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ ብዙ ፈተናዎች ውስጥ መሠረቷን ሳትለቅ አጋጥሟት የነበረውን ከባድ ፈተና አልፋለች ነው ያሉት ።

በቀጣይም ወቅታዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረጉ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ በመሥራት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ያሰገነዘቡ ሲሆን፥ በቀሪ የበጀት ዓመቱ ወራትም በዋናው መሥሪያ ቤት፣ በተጠሪ ተቋማት እና ሚሲዮኖች የተናበበ ሥራ በመስራት የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም አስጠብቆ መጓዝ ይገባል ነው ያሉት።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው÷ በአሁኑ ወቅት የዓለም ጂኦ ፖለቲካ በተለያዩ ጎራዎች እያለፈ መሆኑን በማንሳት ፥ ኢትዮጵያ እያንዳንዱን ርምጃዋን ከብሔራዊ ጥቅሟ አኳያ እየመዘነች ምክንያታዊ እና የተሰላ ስትራቴጂካዊ አካሄድ እየተከተለች ነው ብለዋል።

 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ÷ሀገራዊ የለውጥ ማሻሻያውን መሠረት በማድረግ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ራሱን በመፈተሽ ባለፉት 9 ወራት ስኬታማ ማሻሻያ ማድረጉን መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.