የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጥገና ክፍል ቦይንግ 767 የመንገደኛ አውሮፕላንን ሙሉ በሙሉ ወደ እቃ ጫኝነት የመቀየር ስራን በስኬት አገባደደ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን ጥገና ክፍሉ ከእስራኤል ኤሮስፔስ ኢንደስትሪስ (IAI) ጋር በጥምረት ቦይንግ 767 የመንገደኛ አውሮፕላንን ሙሉ በሙሉ ወደ እቃ ጫኝ አውሮፕላን የመቀየር ስራ በተሳካ ሁኔታ ማገባደዱን አስታወቀ።
ዓየር መንገዱ ስኬታማ ክንውን ያለውን ይህንን ስራ አስመልክቶ እስካሁን ስለተገኘው ውጤት ማብራሪያ የተሰጠበት መርሃ ግብርን በትናንትናው እለት አከናውኖ ነበር።
በቀጣይ ሁለት ወራት አውሮፕላኑን ሙሉ በሙሉ ወደ እቃ ጫኝ የመቀየሩ ተግባር ሲጠናቀቅ የአየር መንገድ የጥገና ክፍል በአፍሪካ ደረጃ የመንገደኛ አውሮፕላንን ሙሉ በሙሉ ወደ እቃ ጭነት አውሮፕላን የቀየረ የመጀመሪያው የጥገና ማዕከል እንደሚያደርገው ነው የተገለፀው።
በመርሃ ግብሩ ላይ በኢትዮጵያ የእስራኤልአምባሳደር አለልኝ አድማሱ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች መገኘታቸውን ከዓየር መንገዱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።