ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ በግንባታ ላይ የሚገኘውን የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ከከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር በመሆን በግንባታ ላይ የሚገኘውን የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ ፕሮጀክትን ጎብኝተዋል፡፡
ፋብሪካው ግንባታው ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር በቀን 10 ሺህ ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ያለው ሲሆን፥ በኢትዮጵያ ትልቁ የሲሚንቶ ፋብሪካ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ጉብኝቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
ቅድሚያ በተሰጣቸው የማዕድን፣ ግብርና፣ ቱሪዝምና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ የግሉ ዘርፍ ልማት የአካባቢውን ኢኮኖሚው በይበልጥ እንደሚያሳድግ ይጠበቃልም ብሏል ፅህፈት ቤቱ።
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው፥ “ሀገራዊ የአቅርቦት ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የምንችለው የማምረት አቅማችን በብዛት፣ በጥራት እና በፍጥነት ማደግ ሲችል ነው” ብለዋል።
የምርት አቅርቦት እንዲያድግም በመንግስት አቅም ከሚሰሩት በተጨማሪ የግሉን ዘርፍን በሰፊው ማሳተፍ እንደሚጠይቅም ነው ያወሱት።
ተጨማሪ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን በሃገር በቀልና በውጭ ኩባንያዎች እንዲገነቡ በማድረግ የሲሚንቶ አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ ኢንጂነር ታከለ ጠቁመዋል።