Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ ዕርዳታ ያለምንም ገደብ ወደ ትግራይ ክልል እንዲደርስ እያደረገ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ ዕርዳታ ያለምንም ገደብ ወደ ትግራይ ክልል እንዲደርስ እያደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በመንግስት በቅርቡ ሰላም የማስፈን ውሳኔ ከተላለፈ ዕለት ጀምሮ 146 የሰብዓዊ ድጋፍ የጫኑ ተሽከርካሪዎች እና 9 ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች ወደ ትግራይ ክልል መግባታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት መግለጫ÷ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ሰብዓዊ ዕርዳታዎች ያለምንም ገደብ ወደ ክልሉ እንዲደርሱ እየተሰራ ቢሆንም÷ህውሓት ችግር ከመፍጠር እንዳልተቆጠበ ተናግረዋል።

የውጭ አገራት ለጋሾች እጅ ማጠር እና በሃገር ውስጥ የተረጅዎች ቁጥር መጨመር በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ህወሐት ከአርቢቲ፣ በረሃሌ እና ከአብአላ ውጭ ከሌሎች በወረራ ከያዛቸው የአፋር አካባቢዎች እንዳልወጣ እና አሁንም ድረስ አንዳንድ የአማራ ክልል ቀበሌዎችን ይዞ እንደሚገኝ ነው በመግለጫቸው ያመላከቱት።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰብአዊ እርዳታዎችን እንዲያደርግና ህወሓት በኃይል ከያዛቸው አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣ ግፊት ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ህወሓት በዚህ ሰዓትም ጥቃት ሊፈፅም እንደሚችልም ዛቻ መሰል መልዕክት እያስተላለፈ እንደሚገኝ አምባሳደር ዲና አመልክተዋል።

እስካሁን ከ15 ሺህ 300 በላይ ዜጎች ከሳዑዲ እንደተመለሱ ጠቅሰው÷“ ከኢድ እስ ኢድ„ ወደ ሃገር ቤት መርሃ ግብር ዳያስፖራው ዘመድ እንዲጠይቅ፣ የኢትዮጵያን ባህላዊ እና ታሪካዊ መስህቦች እንዲያስተዋውቅ እና ለሀገር ልማትና ሰላም የበኩላቸውን እንዲወጡ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

ከኢድ እስከ ኢድ በሚል የተጀመረው መርሃ ግብር በአሁኑ በዓል ብቻ የሚቆም ሳይሆን በቀጣይም በተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ህዝባዊ በዓላት ላይ ዜጎች ለአገራቸው የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ በቀጣይነት እንዲከናወን የሚደረግ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አክለውም÷ የኬንያው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙዋይ ኪባኪ ህልፈትን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በስርዓተ ቀብራቸው ለመገኘት ወደ ቦታው ማቅናታቸውን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከአፍሪካ መድሃኒት አቅራቢ አጀንሲ ጋር መድሀኒቶች በተሻለ ጥራት እንዲሸጡ እና ተአማኒ እንዲሆኑ በሚያስችል ጉዳይ ላይ 29ኛ አገር ሆና መፈራረሟን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ እና በሱዳን ያለውን የድንበር ጉዳይ ችግር ለመፍታት÷ በሁለቱ አገሮች የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት የጋራ ኮሚሽኖች እየሰሩ ነው ብለዋል።

በወንድወሰን አረጋኸኝ እና በይስማው አደራው
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.