Fana: At a Speed of Life!

በጎንደር የተፈጠረውን ክስተት ተከትሎ ግጭትን ለማስፋፈት እየሰሩ ያሉ የግጭት ነጋዴዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መንግስት አሳሳበ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 21 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎንደር ከተማ የታየው እና ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲስፋፋ እየተሰራ ያለው አሳፋሪ ተግባር በክርስትናም ሆነ በእስልምና ሃይማኖት ተቀባይነት እንደሌለው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም መንግስት የግጭቱ ምክንያት ምንም ይሁን ምን ተግባሩ የሚወገዝና ተቀባይነት የሌለው አሳፋሪ ተግባር ነው ብሎ እንደሚያምን ተናግረዋል።
ህዝቡ የግጭት ነጋዴዎች የሚያተርፉት አንዱን ከአንዱ በማጋጨት መሆኑን በመረዳት ከግጭት አባባሽ ተግባራት እንዲቆጠብም ጥሪ አቅርበዋል።
ግጭትን ለማስፋፋት የሚደረገውን የትኛውንም እንቅስቃሴ መንግስት አይታገስም ብለዋል።
በደረሰው ጉዳት እጃቸው ያለበት በርካታ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ጠቁመዋል።

ጎንደር ከተፈጠረው ክስተት ጋር በተያያዘ እስካሁን በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ተጨማሪ ግጭት እና ጥፋት እንዲፈጠር እየሰሩ ያሉ አካላት አሉ ያሉት ሚኒስትሩ፥ በዚህ አፍራሽ ተግባር እየተሳተፉ ያሉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።

ችግሩን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት እየሰሩ ያሉ አካላትን መንግሥት እንደማይታገስ በመጥቀስም፥ ወንጀልን በወንጀል ለማካካስ የሚደረግ ማንኛውም ጥረት ከወንጀል ፈፃሚነት ተለይቶ አይታይም ብለዋል።

የአማራን ህዝብ በሃይማኖት፣ በብሔር እና በአካባቢ ለመከፋፈል የሚሰሩ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መንግሥት አሳስቧል።

መላው ህዝብ የጽንፈኞችን ሴራ በመገንዘብ ሴራቸውን ለማክሸፍ ከመንግሥት ጋር በትብብር እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል መንግሥት በአሸባሪው ሸኔ ላይ የተከፈተው ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠሉን እና በዚህም በቡድኑ ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ መድረሱን ገልጸዋል።

ወደ ትግራይ ክልል የዕለት ደራሽ እርዳታ፣ መድሃኒት እና የሕክምና ቁሳቁስ የማጓጓዙ ጥረት በየብስ እና በአየር ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰዋል።

በበርናባስ ተስፋዬ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.