Fana: At a Speed of Life!

ኔቶ አውሮፓን የግጭት ቀጠና ከማድረግ ባለፈ በእስያ ፓስፊክ ቀጠና ከሚያደርገው ትንኮሳ እንዲቆጠብ ቻይና አስጠነቀቀች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አውሮፓን የግጭት ቀጠና ከማድረግ ባለፈ በእስያ ፓስፊክ ቀጠና የሚያደርገውን ትንኮሳ እንዲያቆም አስጠንቅቃለች፡፡

ቻይና ማስጠንቀቂያዋን የሰጠችው የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሊዝ ትረስ÷ በቀጠናው የሚስተዋለውን ግጭት በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ የኔቶን አቅም ማሳደግ ይገባል ሲሉ ለአባል አገራት ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም ሩሲያን በኢኮኖሚና በሌሎች ዘርፎች ከተቀረው ዓለም ለመነጠል አገራት በቅንጅት መስራት አለባቸው፤ ቻይናም በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት መመራት አለባት ሲሉ ነበር ያሳሰቡት።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን በበኩላቸው፥ ኔቶ የአገራትን ሉዓላዊነት ከመጣስ ባለፈ የተለያዩ ጥቃቶችን በመፈጸም ንጽሃንን ለህልፈት እየዳረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቅርቡም በሰሜን አትላንቲክ የሚንቀሳቀሰው ኔቶ ወደ እስያ ፓስፊክ ቀጠና በማቅናት ጦር እየሰበቀ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ተቋሙ አውሮፓን የግጭት ቀጠና እያደረጋት ነው ያሉት ሚኒስትሩ ፥ አሁን ላይ በእስያ ፓስፊክ የሚያደርገው ትንኮሳም በቀጠናው ብሎም በዓለም አላስፈላጊ ግጭት ለማነሳሳት ያለመ ነው ብለዋል፡፡

ስለሆነም አውሮፓ አሁን ላይ ለደረሰችበት ውጥረት ዋነኛ ምክንያት የሆነው ኔቶ በእስያ ፓስፊክ ቀጠና ከሚያደርገው አላስፈላጊ ትንኮሳ እንዲቆጠብ አስጠንቅቀዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.