ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ከፈረንሳይ የአገር ውስጥ ሚኒስትር እና በኬኒያ የኢንተርፖል ሃላፊ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ከፈረንሳይ የአገር ውስጥ ሚኒስትር፣ የዲሲ አይ ኤስ ትብብር ቢሮ ኃላፊ ጂን ክሪስቶፍ ሂላሪ እና በኬኒያ የኢንተርፖል ሃላፊ ጌዲዮን ኪሚሉን ጋር ተወያይተዋል።፡
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖል፣ ከሮክና ሲቪ ፖል ጋር በመተባበር ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም በወንጀል ድርጊት ተፈላጊዎችን ለፍትህ ለማቅረብ በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም የተጀመሩ የጋራ ዘመቻዎች እና የምርመራ ስራዎችን አጠናክሮ የማስቀጠል ስራ እንደሚከናወን ነው የተናገሩት፡፡
ጂን ክሪስቶፍ ሂላሪ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር የተሰሩ ዘመቻዎች ውጤታማ በመሆናቸው ግንኙነታችንን ወደ ፊት በበለጠ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
ጌዲዮን ኪሚሉ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ምስራቅ አፍሪካን ከወንጀል ነፃ ቀጠና ለማድረግ በግዳጅ ላይ ለተሰማሩ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መኮንኖችና አባላት በዲጅታል የፖሊስ መገናኛ ሬዲዮ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ተቋሙ በጠንካራ አመራር እየተመራ መሆኑን ተረድቻለው ያሉት ኃላፊው÷ ኢትዮጵያ የቀጠናውን ሰላም ለማረጋገጥ ጠንክራ እንደምትሰራ እተማመናለሁ ማለታቸውን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።