ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ በጽንፈኛ ሀይሎች የሚደርሰውን ጥቃት አንታገስም – የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 21 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ በጽንፈኛ ሀይሎች የሚደርሰውን ጥቃት እንደማይታገስ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል አስታወቀ።
የክልሉ መንግስት በወቅታዊ ክልላዊ ሁኔታ ላይ መግለጫ ሰጥቷል።
የመግለጫው ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው
የተጀመረው የለውጥ ጉዞ በጸረ ሰላም ሀይሎች ፈጽሞ ሊደናቀፍ አይችልም።
ከዚህ ቀደም የነበረው የጭቆና አገዛዝ በህዝብ ትግል ተወግዶ በአዲስ መንፈስ እና በአዲስ አስተሳሰብ የህዝባችንን የመልማት፣የማደግ እና የመለወጥ ፍላጎት ለማሟላት የለውጡ መንግስት በሁሉም ዘርፍ እየተጋ ይገኛል።
በሀገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ያላስደሰታቸው እና የግል ጥቅማቸው ተነካብን ብለው የሚያስቡ ቡድኖች የህዝቡን ሰላም ለማደፍረስ ሌት ተቀን እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
በክልላችን በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጠሩ የነበሩትን የፀጥታ ችግሮች የክልሉ መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀትና አስፈላጊውን የህግ ማስከበር ስራ በመስራት የከፋ አደጋ እንዳይደርስ ሲያደርግ ቆይቷል።
ሰሞኑን በሚያሳዝን ሁኔታ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ሀይማኖትን ሽፋን አድርጎ እየተካሄደ ያለው ግጭትና ጥቃት ለሀገርም ሆነ ለሁሉም ቤተ እምነት ተከታዮች የሚበጅ እንዳልሆነ ሁሉም ወገን ሊገነዘበው ይገባል።
ቁጥራቸውና አደገኛ ሴራቸው እየበረከተና እየተራቀቀ የመጣው የሀገራችን ጠላቶች በብሄር ጽንፍ የከፈቱትን ዘመቻ ተጨማሪ መልክና ገጽታ ለማላበስ ወደ ቤተ እምነቶች ፊታቸውን አዙረዋል።
ህብረተሰቡ በቤተ እምነቶችም ሆነ በምዕመናን ላይ የሚፈጸምን ጥቃት ማውገዝ ብቻ ሳይሆን የመከላከል ሃላፊነት አለበት።
በተለይም ድርጊቱን የእምነትም ሆነ የብሄር ተምሳሌት ወደ ሆነው ክልላችን ለማምጣት የሚደረገው ሙከራ በህዝቡ የተባበረ ክንድ ለማክሸፍ ህዝቡ እጅ ለእጅ ተያይዞ መንቀሳቀስ ይጠበቅብታል።
ህዝቡ በብዙ መልኩ ተጋምዶ የኖረውን ሙስሊምና ክርስቲያን በደም ለማቃባት ብሎም ሀገር ለማፍረስ የሚደረገውን የፖለቲካ ሸፍጥ በአግባቡ ተገንዝቦ ይህን የሚመጥን አዎንታዊ ሚና መጫዎት ይጠበቅበታል።
ትላንት ሚያዝያ 20/2014 ዓም በስልጤ ዞን በወራቤ ከተማ እና በሳንኩራ ወረዳ ላይ በሀይማኖት ተቋማት ላይ ያነጣጠረው ጥቃት ለዘመናት ተቻችለው እና ተከባብረው በኖሩ የልዩ ልዩ እምነት ተከታይ ህዝቦች ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው።
ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ በጽንፈኛ ሀይሎች የሚደርሰውን ጥቃት የክልሉ መንግስት የማይታገስ ሲሆን በስልጤ ዞን የተጀመረው ጥቃት ወደ ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች እንዳይዛመት ሰላም ወዳዱ የክልላችን ህዝብ ከመንግስት ጎን በመሆን የአካባቢውን ሰላም ማስጠበቅ ይኖርበታል።
የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የክልሉ መንግስት በትኩረት የሚሰራ ሲሆን በሀይማኖት ተቋማት እና በንጹሀን ዜጎች ላይ ጥቃት በሚፈጽሙ አካላት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አመራሮች ላይ አስፈላጊውን ህግ የማስከበር እርምጃ በመውሰድ ተጠያቂ እንዲሆኑ ያደርጋል።
ወጣቶች የጸረ ሰላም ሀይሎችን እኩይ ተግባር ማስፈጸሚያ ከመሆን ተቆጥበው የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸውም የክልሉ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል።
ወጣቶች የሀገራችን እድገት ያላስደሰታቸው አካላት ከዘረጉት የሴራ ወጥመድ ተላቀው ለዘመናት በመቻቻል እና በመከባበር ላይ የተገነባውን የህዝቦች አንድነት ማስጠበቅ ይገባል።
በየደረጃው የሚገኙ የሀይማኖት አባቶች፣የሀገር ሽማግሌዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች የጥፋት ሀይሎችን ሴራ በማውገዝ የአካባቢያቸውን ሰላም እና ደህንነት ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል።
የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል መንግስት።