በጎንደር ከተማ በተከሰተው ችግር ከ370 በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 21 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎንደር ከተማ አስተዳደር በተከሰተው ችግር 373 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው አስታውቀዋል።
ጎንደር ያለ ታሪኳና ያለ ባሕሏ ችግር መከሰቱን አስታውሰው፥ ጎንደር ላይ በተፈፀመው ችግር ምክንያት ችግሮቹን እንዲሰፉ የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን ገልፀዋል።
ጥፋተኞቹን የመያዝ ተግባርም እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመወያየት ወደ ሰላም ከተመለሰ በኋላ ትናንት እንደገና እኩይ ዓላማቸውን ለማስፈጸም ፍላጎት በነበራቸው አካላት በተነሳ ግጭት የሰው ሕይወት ማለፉንና ንብረት መውደሙንም ነው የተናገሩት።
ትናንት ዳግም ግጭት ለመቀስቀስ የሞከሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ገልፀዋል።
በተወሰደው እርምጃ ጎንደር ወደ ሰላም እየተመለሰች መሆኑን ጠቅሰው፥ አስተማማኝ የሚሆነው ግን በጥፋት የተሳተፉትን በሙሉ ለቅመን ስንይዝ ነው ብለዋል።
ይሕ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የፀጥታ ኃይሉ በሠራው ሥራ 373 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል።
ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የፀጥታ ኃይሎችንና መሪዎችን በሕግ ተጠያቂ እየተደረገ መሆኑንም አመላክተዋል።
የፀጥታ ኃይሉ በተቀናጀ መንገድ እርምጃ እንዲወስድ አቅጣጫ መቀመጡንም አውስተው፥ ኃላፊነቱን ያልተወጣ ሁሉ ይጠየቃልም ነው ያሉት።
ተጠርጣሪዎች ተለቅመው እስኪያዙ ድረስ ከፀጥታ ኃይሉ ውጭ ያለው መሣሪያ እንዳይወጣ አቅጣጫ ተቀምጧል።
የፀጥታ ኃይሎችን ልብስ ከአባል ውጭ ለብሶ በሚገኝ አካል ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም ገልፀዋል።
ከከተማ የሚወጣም ሆነ የሚገባ መሣሪያ እንዳይኖር መታገዱን ጠቁመው፥ ከሕዝብ ጋር የሚቆሙትና ለሕዝብ መስዋዕትነት የሚከፍሉ የራሳቸው ትጥቅ ያላቸው ጀግኖች ፋኖዎች ከመንግሥት ሥምሪት እስከሚሰጣቸው ድረስ በቤታቸው ሆነው እንዲጠብቁም ጥሪ አቅርበዋል።
በፋኖ ስም በሚነግድ አካል ግን አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት ኃላፊው።
ለአንድ ወገን በማድላት ችግር እንዲባባስ የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።