Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ከተማ የጎዳና ላይ የኢፍጣር መርሐ ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ከተማ የረመዳን ጾምን ምክንያት በማድረግ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የተሳተፉበት የጎዳና ላይ የኢፍጣር መርሐ ግብር ተካሂዷል።
ኢፍጣሩን ከታደሙት መካከል ሼህ ዛኪር ኢብራሂም÷ በእስልምና ዕምነት አስተምህሮ ከወራቶች ሁሉ በላጩና ታላቅ የኢባዳ ወር የሆነው የረመዳን ፆም ወቅትን ህዝበ ሙስሊሙ ሲያሳልፍ አቅመ ደካሞችንና ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በማሰብና በመርዳት መሆን አለበት ብለዋል።
በዚሁ በተከበረው የረመዳን ወር ያጡና የተቸገሩ አቅመ ደካማ ወገኖችን በዘላቂነት የምንረዳበት ሊሆን እንደሚገባ አስረድተዋል።
ሌላው ኢፍጣሩን የተካፈሉት አቶ ኡሞድ ኝጎዎ በበኩላቸው የተቀደሰውን የኢባዳ ወር ስናሳልፍ አቅም የሌላቸው ምስኪኖችን በማሰብና በመርዳት ሊሆን እንደሚገባ አመላክተዋል።
የረመዳን ወርን በመተጋገዝና በመረዳዳት እያሳለፉ እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ኡሞድ ከረመዳን÷ በኋላም የመተሳሰብ እሴት ሃይማኖቱ በሚፈቅደው ሁሉ አጠናክረው ለመቀጠል ቃል ገብተዋል።
የረመዳን ወር በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የእዝነትና የራህመት እንዲሁም ይቅር የምንባባልበት ወር እንደመሆኑ በቀጣይም እምነቱ የሚያዘውን መተግበር ከሁላችንም ይጠበቃል ያሉት ደግሞ ሸህ መሀመድ መኪን ናቸው።
የጎዳና ላይ ኢፍጣሩ በከተማው ለመጀመሪያ ጊዜ መካሄዱን ጠቁመው በቀጣይም አቅመ ደካሞችን በመርዳት ሊሆን እንደሚገባ መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.