Fana: At a Speed of Life!

ባለሥልጣኑ የጥላቻ ንግግር በሚያሠራጩ የመገናኛ ብዙኃን ላይ እርምጃ እንዲወስድ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 21 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የጥላቻ ንግግር በሚያሠራጩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ላይ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።
በምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን መሥሪያ ቤትን የ2014 በጀት ዓመት የ9 ወር የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ዕጸገነት መንግሥቱ የአገሪቷን አጠቃላይ ሁኔታ እና ታሪካዊ ዳራ የሚመጥን የሚዲያ አውታር ተገንብቶ እንደማያውቅ ጠቅሰው፥ በቀጣይ ግን ሀገሪቱን የሚመጥን፣ የሙያዊ ክህሎት ክፍተት የማይንጸባረቅበት፣ የሙያውን ሥነ-ምግባር ያከበረ የመገናኛ ብዙኃን አውታር መገንባት አለበት ብለዋል።
የመገናኛ ብዙኃን በገለልተኛነት የዴሞክራሲ ባህል እንዲያብብ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተመጣጣኝ መረጃ እንዲዳረስ፣ መረጃ አሠረጫጨቱም ተጠያቂነት ያለበት እንዲሆን፤ ባለሥልጣኑ በትኩረት እንዲሠራም አመላክተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ኢትዮጵያን በተመለከተ የተዛባ መረጃ እንዲሁም የጥላቻ ንግግር ሲያሠራጩ የነበሩትን የውጭ መገናኛ ብዙኃን ወኪሎች ከማጋለጥ አኳያ ባለሥልጣኑ የሄደበትን ርቀት አድንቀዋል።
የተሳሳቱ መረጃዎችን በማሠራጨት ረገድ፣ ወቅታዊ እና ትኩስ መረጃዎችን ተደራሽ ካለማድረግ፣ ሚዛናዊነትን ካለመጠበቅ፣ ስሜታዊነት እና ወገናዊነት የሚንጸባረቅባቸውን አቀራረቦችን ከማዘውተር አኳያ ባለሥልጣኑ ሥራዎች ይጠበቅበታል ማለታቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ኢድሪስ ቋሚ ኮሚቴው በድክመት ያነሳቸውን ጉዳዮች በትኩረት እንደሚሰሩባቸው ተናግረዋል።
ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ሆኖ ሐሰተኛ መረጃ ሲያሠራጩ የነበሩት የውጭ ሚዲያ ወኪሎች የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደተሰጣቸውም አስረድተዋል።
ከዚህ ባለፈም የዕውቅና ፈቃድ እንዲሰረዝ መደረጉንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.