Fana: At a Speed of Life!

የዓለም የምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል በከባድ ሁኔታ ውስጥም እያደረገ ያለው የሰብአዊ እርዳታ የሚያስመሰግን ነው – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን በቅርቡ አዲስ ከተሾሙት የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተጠሪ ዳይሬክተር ክላዉድ ጂቢዳር ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።

አቶ ደመቀ የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተሻለ ሥራዎችን ማከናወኑን ለዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል በከባድ ሁኔታ ውስጥም እርዳታ ለሚሹ ዜጎች እያደረገ ያለው ሰብአዊ እርዳታ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል ።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ያሉት አቶ ደመቀ፥ እንደ ዓለም ምግብ ፕሮግራም ያሉ ድርጅቶች ደግሞ ሁሉን አቀፍ ተደራሽ የሆነ ሰብአዊ እርዳታ በማድረግ የተጠናከረ ድጋፍ እንዲያደርጉ እንፈልጋለን ነው ያሉት።

በትግራይ ክልል እየሰጠው ካለው ሰብአዊ እርዳታ በተጨማሪ በአማራ እና በአፋር ክልልም እንዲሁም ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎችም ተመሳሳይ ሥራ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

አቶ ደመቀ መንግሥት ያልተገደብ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደረግ ያሳለፈውን ውሳኔ በማክበር የተሻለ ድጋፍ እንዲደረግ እየሰራ መሆኑን አንስተው፥ የህወሓት ቡድን ግን አሁንም ሰብአዊ እርዳታውን ለማስተጓጎል እየሞከረ ነው ብለዋል ።  ዓለም አቀፍ ለጋሽ አካላትም የቡድኑን አካሄድ ማውገዝ አለባቸው ነው ያሉት።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተጠሪ ዳይሬክተር ክላዉድ ጂቢዳር በበኩላቸው የመንግሥትን ቁርጠኝነት በማድነቅ በቀጣይም አብሮ ለመስራት በሙሉ ቁርጠኝነት እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ከችግር ውስጥ ወጥቶ ወደ ተሻለ መንገድ እና እድገት መስመር መግባት ከራሷም በላይ ለሌሎች ሀገራትም ትልቅ ሚና ስላለው ከመንግስት ጎን ሆነን ችግሩን ለማለፍ እንሰራለን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች የውስጥ መፈናቀል ካጋጠማቸው ዜጎቿ በተጨማሪ ከ9መቶ ሺህ በላይ ስደተኞችን እያስተናገደች መሆኗን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

የምግብ አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ ኢትዮጵያ ስንዴን በከፍተኛ መጠን የማምረት አቅም ያላት ሀገር በመሆኗ ለዚህ ተግባር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም የሚያደርገውን የሰብአዊ ድጋፍ በድርቅ ወደ ተጎዱ አካባቢዎችም እንደሚያስፋፋ ተናግረዋል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.