Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሰላም እንዲመጣና በግጭት የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን ገለፀች

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)  የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በቢሯቸው በኩል በኢትዮጵያ ግጭቶችን ለማስቆም እየተካሄዱ የሚገኙ ተግባራዊ ስራዎችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

አሸባሪው ህወሃት በፈጠረው ጦርነትና በወረራ በያዛቸው አካባቢዎችን እንዲሁም በተለያዩ ግጭቶች የተነሳ ብዙሃን ለችግር መጋለጣቸውን ያስታወሰው መግለጫው ይህንን ችግር ለመቅረፍ በፌደራል መንግስትና በክልሎች የተወሰደውን እርምጃ አድንቋል።

በተለይም በትግራይና አፋር ክልሎች በችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሰብአዊ ድጋፎች እንዲደርሳቸው ለማስቻል የተከናወኑ ተግበራትን ያደነቁት ብሊንከን፤ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንም ያልተቋረጣ አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ በግጭት ለተጎዱ ወገኖች እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውን ተናግረዋል።

አሜሪካም በዚህ ሂደት ውስጥ ድጋፋን ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን መግለጻቸውን ከሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ቢሮ የተገኘው መግለጫ ያመለክታል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ሰላም እንዲመጣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተወሰዱ እርምጃዎችን ያደነቀው መግለጫው በትግራይ ክልል ነገሮችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ ጥረቶች እንዲጠናከሩ መጠየቃቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለከትል።

አንድነቷ፣ ሉዓላዊነቷና እድገቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ለሚከናወኑ ተግባራት አሜሪካ ድገፏን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን መግለጫው አመልክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.