የኢድ-አልፈጥር በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር ተከብሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ የጋራ ግብረ ኃይሉ ዝግጅቱን አጠናቆ ተልዕኮውን በቁርጠኝነት እየተወጣ እንደሚገኝ አስታወቀ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢድ-አልፈጥር በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር ተከብሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ የጋራ ግብረ ኃይሉ ዝግጅቱን አጠናቆ ተልዕኮውን በቁርጠኝነት እየተወጣ እንደሚገኝ አስታወቀ።
የጋራ ግብረ ኃይሉ የኢድ-አልፈጥር በዓል የመልካም ምኞት መግለጫ አውጥቷል።
በየትኛውም እምነት ውስጥ ተደብቀው እምነቱ ከሚፈቅደው ውጭ የተለያዩ ፀረ-ሰላም እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ቡድኖችንና ግለሰቦችን ህዝቡ ከውስጡ አውጥቶ በማጋለጥ ለፀጥታ አካላት አሳልፎ በመስጠት የተለመደውን ቀና ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልና ሀገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ የጋራ ግብረ ኃይሉ ጥሪ አቅርቧል።
የግብረኃይሉ ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፦
የፌደራል ፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ለእስልምና ዕምነት ተከታዮች እንኳን ለኢድ-አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ እያለ የመልካም ምኞት መልዕክቱን ያስተላልፋል
በሀገር አቀፍ ደረጃ ባለፈው ሳምንት ተከብሮ ያለፈው የፋሲካ በዓል እና በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ የተዘጋጀው ታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሃ ግብር በሰላማዊ መንገድ ተካሂደው በሰላም ተጠናቋል።
በመሆኑም ከጥምር የፀጥታ አካላት የተሰጠውን መመሪያ ከግምት ውስጥ በማስገባት አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ላደረጋችሁ የሁሉም ሀይማኖት አባቶች፣ በዓሉን በኮሚቴነት ያስተባበራችሁና የመራችሁ አካላት፣ ምዕመናኑን በማስተናገድ ከፍተኛ ድርሻ የተወጣችሁ ወጣቶችና ሰላም ወዳዱ የሀገራችን ህዝብ እንዲሁም በዓላቱ በሰላም እንዲጠናቀቁ የራሳችሁን ድርሻ ላበረከታችሁ የፌዴራልና የክልል የፀጥታና ደህንነት ኃይሎች በሙሉ የፌደራል የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ላቅ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡
ከፋሲካ በዓል በፊትም ሆነ ከትንሳኤ ጋራ በተያየዘ የተደረጉ የአምልኮት ስርዓቶች እና የኢፍጣር መርሃ ግብር ሁሉ የኢድ-አልፈጥር በዓልም በተመሳሳይ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲጠናቀቅ የጋራ ግብረ ኃይሉ ዝግጅቱን አጠናቆ ተልዕኮውን በአዲስ አበባና በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች በቁርጠኝነት እየተወጣ ይገኛል፡፡
ይሁን እንጂ መንግስት ለበዓላቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ባለበት በዚህ ወቅት ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ አንዳንድ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ህዝቡን ለማሳሳትና የእምነቶቹ ወግና ሥርዓት ከሚፈቅደው ውጪ ምዕመናኑን ወደ ግጭት ለማስገባት እንቅስቃሴ እያደረጉ እንዳሉ የጋራ ግብረ ኃይሉ ደርሶበታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ ከቀብር ቦታ ጋር በተያያዘ በተወሰኑ የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የተነሳ ግጭት የተቀሰቀሰ ቢሆንም ግጭቱን በሀይማኖት ሽፋን ለማባባስ የሚደረገው ጥረት እኩይ ዓላማ ላላቸው ፀረ-ሰላም ኃይሎች ዕድል ስለሚፈጥር ሁሉም የሀይማኖት ተቋማት ይህንን ተገንዝባችሁ አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ እየተሰራ ያለውን ተግባር ማገዝ ይጠበቅባችኋል ።
በተመሳሳይ በስልጤ ዞን በወራቤ ከተማ ግጭቱን ለማባባስ በተናበበ በሚመስል አኳሃን በቤተ እምነት ላይ የደረሰው ቃጠሎ እና በክቡር የሰው ልጅ ህይወት ላይ የደረሰው ሞት የክርስትናንም ሆነ የእስልምናን እምነቶች የማይወክል ተግባር ነው።
በዚህ አጋጣሚ በጎንደርና በወራቤ ከተሞች በጠፋው ክቡር የሰው ልጅ ህይወት እና በእምነት ተቋማቱ ላይ በደረሰው ውድመት የጋራ ግብረ ኃይሉ የተሰማውን ልባዊ ሀዘን ይገልፃል።
ከዚሁ ሁከትና ብጥብጥ ጋር በተያያዘ ከሁለቱም ወገን በድርጊቱ ውስጥ የተሳተፉ እንዲሁም ከጀርባ ሆነው ግጭቱ እንዲባባስና ወደ ሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች እንዲዛመት ሲቀሰቅሱና ሲያነሳሱ የነበሩትን ፀረ-ሰላም ኃይሎችን እንዲሁም ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠርና እንዲስፋፋ በማህበራዊ ትስስር ገጿች የሃሰት መረጃዎችን ያሰራጩና እያሰራጩ ያሉትንም ጭምር የጋራ ግብረ ኃይሉ እያደነ ለህግ ማቅረቡን እንደቀጠለ ይገኛል፡፡የጋራ ግብረ ኃይሉ በዚህ ዙሪያ በቀጣይ ሰፊ መግለጫ ይሰጥበታል፡፡
በየትኛውም እምነት ውስጥ ተደብቀው እምነቱ ከሚፈቅደው ውጭ የተለያዩ ፀረ-ሰላም እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ቡድኖችንና ግለሰቦችን ህዝቡ ከውስጡ አውጥቶ በማጋለጥ ለፀጥታ አካላት አሳልፎ በመስጠት የተለመደውን ቀና ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልና ሀገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ የጋራ ግብረ ኃይሉ ጥሪውን ያቀርባል።
የህዝብን ሰላምና ደህንነት የሚያውኩ የፀረ-ሰላም ቡድኖችና ግለሰቦች ከዚህ እኩይ ድርጊታቸው የማይታቀቡ ከሆነ የፌደራል የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ከክልል መንግስታትና የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የጀመረውን ህግ የማስከበር ተግባሩን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ያረጋግጣል።
በድጋሚ እንኳን ለዳግም ትንሣኤ እና ለዒድ አል-ፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡
በዓሉ የሰላም፣ የጤና እና የፍቅር እንዲሆንላችሁ የጋራ ግብረ ኃይሉ ከልብ ይመኛል።
ዒድ-ሙባረክ !
ሚያዚያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም
በ 987 እና 991 ነፃ የስልክ መስመሮችን በመጠቀም መረጃ ያድርሱን