Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ከመኖሪያ ቤት ጀርባ በማገዶ እንጨት ተሸፍኖ በድብቅ የተቀመጠ 10 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ በፖሊስ ተያዘ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በጋራ ባደረጉት ክትትል በቦሌ ክፍለ ከተማ ከመኖሪያ ቤት ጀርባ በማገዶ እንጨት ተሸፍኖ በድብቅ የተቀመጠ 10 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ተያዘ።
ከህብረተሰቡ በተገኘው ጥቆማ መነሻነት በተደረገ ክትትል በቁጥጥር ስር የዋለው 7 ባለሰደፍ እና 3 ታጣፊ ክላሽን-ኮቭ ጠመንጃዎች መሆናቸውን ፖሊስ አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ እንዳስታወቀው የጦር መሳሪያው የተያዘው በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 አቦ መሻገሪያ መቃብር ጀርባ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከሚገኙ መኖሪያ ቤቶች በአንዱ ከቤቱ ጀርባ በሚገኝ የማገዶ ማስቀመጫ ስፍራ ላይ በሸራ ተጠቅልሎ በእንጨት ተሸፍኖ በድብቅ በተቀመጠበት ነው።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ አንድ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገ ሲሆን፥ ህብረተሰቡ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በህዝብ እና በሃገር ላይ የሚያመጣውን የደህንነት አደጋ ተገንዝቦ ወንጀሉን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ ጥቆማ እና መረጃ በመስጠት እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.