Fana: At a Speed of Life!

ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ በጎንደር የተፈጠረው ክስተት የክርስትናንም ሆነ የእስልምና እምነቶችን አይወክልም- የጎንደር ከተማ አስተዳደር

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎንደር ከተማ ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ የተፈጠረው ክስተት የክርስትናንም ሆነ የእስልምናን እምነቶች እንደማይወክል የጎንደር ከተማ አስተዳደር ገለጸ፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ ወቅታዊ የጎንደር ከተማ ጉዳይን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸው፥ ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ በከተማዋ በተፈጠረው አሳዛኝ ክስተት ማዘናቸውን ገልጸው፥ በተፈፀመው ድርጊት ወጣቶች፣ አረጋውያን እና የሀይማት አባቶችም አዝነዋል፤ ተፀፅተዋልም ብለዋል።

ይህ የጎንደር መገለጫ አይደለም ያሉት አቶ ዘውዴ ÷ የከተማው ነዋሪና ማህበረሰብም ድርጊቱን እያወገዙት መሆኑን አንስተዋል፡፡

አሁን የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በሀይማኖት አባቶች ዘንድ ውይይት መደረጉን እና ከተማዋ መረጋጋት ላይ መሆኗን ተናግረዋል።

የበለጠ አስተማማኝ ለማድረግም እስከ ቀበሌ ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፥ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ከ373 በላይ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን አመላክተዋል፡፡

ከሁከቱ ጀርባ ያሉትንም ግለሰቦች የመያዝ ስራ ይቀጥላል ሲሉ በመግለጫው ተናግረዋል።

የፌደራልና የክልል የፀጥታ መዋቅሩ ህግ የማስከበር ስራ እየሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡

ማህበረሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ ከሚተላለፉ የተሳሳቱ መረጃዎች ራሱን እንዲጠብቅም ነው ያሳሰቡት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.