ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ለእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ማዕድ አጋሩ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ በተገኙበት ለእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ማዕድ አጋርተዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ የማዕድ ማጋራት ድጋፉን ያደረጉት በአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የአካባቢው የእስልምና እምነት ተከታዎች ነው።
ፕሬዚዳንቷ የማዕድ ማጋራቱን ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ በተገኙበት ማከናወናቸውን
ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ የማዕድ ማጋራት ድጋፉ በቁጥር ደረጃ ጥቂት ቢሆንም የኢትዮጵያውያንን የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴታችን ለሌላው በማሳየትና በማስቀጠል ረገድ የሚኖረውን ሚና በማሰብ የተደረገ ነው ማለታቸውን ከክፍለ ከተማው ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በዚህም ሁሉም ኢትዮጵያውያን ይህንን ፈለግ በመከተል ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ በጋራ ተደጋግፈን ማለፍ ይኖርብናል በማለት ፕሬዚዳንቷ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያውያን የሚያምርብን ፍቅር፣ መከባበርና አብሮ መብላት እንጂ ጠብና ክርክር መገለጫችን አይደለምና አሁን የገጠመንን ፈተና በትዕግስትና አላህን በመፍራት ልናሳልፈው ይገባል ብለዋል።
ህዝበ ሙስሊሙም የተቸገሩ ወገኖችን በማብላትና የተጠሙትን በማጠጣት የተለመደ የመተዛዘንና የመረዳዳት ባህሉን በመተግበር በዓሉን እንዲያከብርም ጥሪ አስተላልፈዋል።