ህዝበ ሙስሊሙ ኢድ አልፈጥር በዓልን ሲያከብር አብሮነትን፣ መደጋገፍንና መቻቻልን በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን ይገባል- አቶ ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)ህዝበ ሙስሊሙ ኢድ አልፈጥር በዓልን ሲያከብር አብሮነትን፣ መደጋገፍንና መቻቻልን በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን ይገባል ሲሉ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ 1443ኛውን የኢድ አልፈጥር በዓል አስመልክቶ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
አቶ ኦርዲን በመልዕክታቸው÷ ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የተጀመሩ በጎ ስራዎችን በማጠናከር ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡
በተለይም ህዝቡ በረመዳን ፆም ወቅት ያሳየውን መደጋገፍና መረዳዳት በማጠናከር እንዲሁም ሰላምንና አብሮነትን በሚያጎለብት መልኩ ማክበር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
የተቸገሩትን በመደገፍ እና የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳት ወገናዊነትን ማሳየት ይገባል ያሉት አቶ ኦርዲን በድሪ÷በክልሉ የኢድ አልፈጥር በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
ለዚህም በክልሉ ከሚገኙ ከሀይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና ከወጣቶች ጋር ውይይት መደረጉን አብራርተዋል፡፡
የክልሉ ህዝብም በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
”ከኢድ እስከ ኢድ’’ መርሐ ግብር አካል የሆነው እና በልዩ ሁኔታ የሚከበረውን የሸዋል ኢድ በዓል እንዲከበር ግብረሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ዲያስፖራም በክልሉ በመገኘት የሸዋል ኢድን በዓል እንዲያከብር ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ከሀረሪ ክልል ኮሙኒኬሽን ያገኘኘው መረጃ ያመላክታል፡፡