Fana: At a Speed of Life!

እንደ ሀገር ያጋጠሙንን ችግሮች ለመሻገር ሙስሊሙ እና ክርስቲያኑ ለዘመናት በአብሮነት መኖራችን ትልቁን አስተዋፅኦ አበርክቷል- ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር ያጋጠሙንን ችግሮች ለመሻገር ሙስሊሙ እና ክርስቲያኑ ማህበረሰብ ለዘመናት በአብሮነት መኖራችን ትልቁን አስተዋፅኦ አበርክቶልን እንዳለፈ መታወቅ አለበት ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ የ1443ኛውን የኢድ- አልፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ ለሕዝበ ሙስሊሙ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም÷ ሕዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወር ያዳበራቸውን መልካም ስራዎች ከረመዳን ውጪ ባሉት ወራትም የተራቡትን በማብላት፣ የታረዙትን በማልበስና የተቸገሩትን በመርዳት እንዲሁም የማዕድ ማጋራቱን ስራ በቀጣይነት በመፈፀም ከፈጣሪው የሚያገኘውን ምንዳ ከፍ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
አክለውም÷ በረመዳን የሰራናቸውን መልካም ተግባራት ሁሉ ከበዓሉም በኋላ ከዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ጋር በማቀናጀት ኢስላማዊ ሰብዕናችንን አድምቀን መታየት ይገባናል ብለዋል፡፡
ከረመዳን ወር ፆም መጠናቀቅ ጋር ግዴታ የሚሆነው ” ዘካተል ፊጥር ” የተደነገገበት የእስልምና ዋና ዓላማ ሁሉም ሙስሊም ድሃ ሰዎችን ከመለመን እንዲድኑና በዕለቱ እንደማንኛውም ሰው እኩል ሆነው የበዓሉ ተካፋይ እንዲሆኑ ለማስቻል መሆኑም ገልጸዋል፡፡
በአሁን ሰአት አገራችን በለውጥ ላይ እንደምትገኝ ሁላችንም እንረዳለን ያሉት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ÷ በሀገራችን ብሄራዊ መግባባትን ለማምጣት የተጀመረውን ጥረት ሁላችንም ልናግዝ ይገባል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ያለንን ፀጋ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅመን የተጀመረውን ለውጥ ለእድገትና ለሰላም እንድናውለው፤ በጥንቃቄና እና በትዕግስት እንድንይዘው በታላቅ አክብሮት እጠይቃለሁም ነው ያሉት፡፡
ሰሞኑን በጎንደር የተከሰተው አስከፊ ሁኔታ ዳግም በሌላ የአገራችን አካባቢ መደረግ ቀርቶ መታሰብ እንደሌለበት ጠቁመው÷ በድርጊቱ የተሳተፉ አካላትም ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል፡፡
በዓሉ የሰላምና የደስታ እንዲሆንልን መልካም ምኞቴን እገልፃሁ “ኢድ ሙባረክ” ሲሉ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.