በጀርመን በተካሄደ የ5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቶች ድል ቀናቸው
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲዳስ ኩባንያ ‘adizero’ በሚል በጀርመን ባዘጋጀው የ5 ኪ.ሜ ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታ አሸንፈዋል።
በጀርመን በተካሄደ የ5 ኪሎሜትር ሩጫ ውድድር በሴቶች÷ አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ 14 ደቂቃ 37 ሰከንድ 2 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ጊዜ በመግባት ነው ውድድሩን በበላይነት ያጠናቀቀችው፡፡
በዚሁ መርሐ ግብር አትሌት መዲና ኢሳ ሁለተኛ በመውጣት ውድድሩን ማጠናቀቋን ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በተመሳሳይ መርሐ ግብር በወንዶች በተካሄደ ውድድር÷ አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ 12 ደቂቃ 53 ሴኮንድ በመግባት አንደኛ ደረጃ በመያዝ አሸንፏል፡፡
አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ ሰሞኑን በቦስተን በተካሄደው የ5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ማሸነፏ ይታወሳል፡፡
በሌላ ውድድር በሴቶች የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር አትሌት ፋንታዬ በላይነህ 30 ደቂቃ 24 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በመግባት ውድድሩን በአንደኝነት አሸንፋለች፡፡
በሴቶች የግማሽ ማራቶን ውድድር ደግሞ አትሌት ትዕግሥት አሰፋ 1 ሰዓት 7 ደቂቃ 28 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በመግባት ውድድሩን በድል አጠናቃለች፡፡