የሀገር ውስጥ ዜና

ታላቁን የኢድ ሰላት በኢትዮጵያ ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁ ተገለጸ

By Melaku Gedif

May 01, 2022

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)   ታላቁን የኢድ ሰላት በኢትዮጵያ ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ የጎረቤት አገራት የሀይማኖት መሪዎች እንዲሁም በአዲስ አበባና አካባቢዋ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት የታላቁ ኢድ ሰላት ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ከኢድ እስከ ኢድ ብሔራዊ ኮሚቴ ሴክሬታሪያትና የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በጋራ ባደረጉት ስብሰባ  አስታውቀዋል፡፡

በወቅቱም የዘንድሮው የዒድ ሰላት ከዚህ በፊት ከነበሩት በተሻለ ቅንጅት ተሰርቶ ለአገር ገፅታ ግንባታ ከፍተኛ ሚና እንዲጫወት የሁሉንም አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል፡፡

ጥሪ የተደረገላቸው የጎረቤት ሀገራት አቻ ተቋማት ተወካዮችም በክብር እንግድነት ለመገኘት ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም በበዓሉ ላይ ለመታደም አስቀድመው መግባት መጀመራቸውም ተጠቁሟል፡፡

የዚህ ዓመት የኢድ ሰላት ስግደት  ከከተማው ሁሉም አካባቢዎች  በመሰባሰብ በጋራ ለመስገድ በሚያስችል መልኩ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚካሄድ መሆኑን ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኮሚቴው ጥሪውን አክብረው  በዓሉ ላይ ለመታደም ለመጡ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች መልካም የኢድ አልፈጥር በዓል እንዲሆን ተመኝቷል፡፡