Fana: At a Speed of Life!

ጠ /ሚ ዐቢይ አሕመድ ለዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 1 ሺህ 443ኛው ዓመተ ሂጅራ የዒድ አል-ፈጥር በዓልን በማስመልከት ለእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም የዘንድሮው ረመዳን በኢትዮጵያ ፍቅርና ሀገራዊ አንድነት የታየበት ሆኖ በማለፉ ከመቼም ጊዜ የተለየ ተደርጎ በታሪክ ሲታወስ ይኖራል ብለዋል፡፡

“ከዒድ እስከ ዒድ” የተሰኘው አገራዊ ንቅናቄም ብዙዎችን ከመላው ዓለም አሰባስቦ በእናታቸው ቤት፣ በወገናቸው መሐል እንዲያሳልፉ ዕድል ፈጥሯል ነው ያሉት።

የቱንም ያህል የሐሳብ ልዩነት ቢኖረን፣ በባህልና በወግ – በቋንቋና በልማድ ብንለያይ፣ ያለን አንድ ሀገር እስከሆነ ድረስ፣ እነዚህ ልዩነቶችን ተሻግረን ወንድማማችና እኅትማማች እንድንሆን፣ እርስ በእርስ እንድንተሳሰብ የፈጣሪ ትእዛዝ ያሳስባል ብለዋል።

በትንሽ በትልቁ እልህና ጠበኝነትን የሚቆሰቁሱ የሸይጣን እጆች በበዙበት በዚህ ወቅት ከሁላችንም የሚጠበቀው ትዕግሥትና ሰከን ብሎ ነገሮችን በጥሞና መመርመር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ የነብዩ መሐመድ ሕይወት አበክሮ እንደሚያስገነዝበን የተመኙትን ለመጨበጥ፣ ከምንም ነገር በላይ ረጋ ብሎ ማሰብን፤ ማሰላሰል እና ትዕግሥት ይጠይቃል ሲሉም አውስተዋል።

የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

 

እንኳን ለዒድ አል ፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

ፈጣሪ ለሰው ልጆች ደስታ ሲል የሰጠውን የዒድ በዓል መላው ሕዝበ ሙስሊም በሐሴት ያከብረዋል። የደስታው ምንጭ መብላት መጠጣቱ፣ መልበስና ማጌጡ አይደለም፤ ከራስ ባለፈ ከሌሎች ጋር በአብሮነት ማሳለፉ እንጂ። ሕዝበ ሙስሊሙ ያሉትን መልካም ነገሮች ይዞ እርስ በእርሱ እየተጠያየቀ፣ አብሮነቱንና አንድነቱን የሚያሳይበት፣ ያለው ከሌለው የሚረዳዳበት፣ ያገኘው ካላገኘው ምግብና ፍቅርን ተጋርቶ የሚያሳልፍበት ዕለት ነው። እነዚህ እሴቶችና የበዓሉ ትሩፋቶች ከእምነቱ ተከታዮች ባለፈ ለሌሎችም መትረፍ የሚችሉ ናቸው።

ከዒዱ አስቀድሞ ሙስሊሙ ወር ሙሉ ከክፋት ርቆ ደግትን ይለምዳል፤ ከዓለማዊ ተግባር ርቆ መልአይካዎችን ይመስላል። መላአክት አይበሉም፤ አይጠጡም፤ በፍጹም ልባቸው የፈጣሪን ትዕዛዝ ይፈጽማሉ። ሕዝበ ሙስሊሙም በረመዳን ወር ከዚህ የተለየ አያደርግም። ወሩ አላህ (ሱወ) እጅግ ውድ ስጦታዎቹን የሰጠበት፣ ቁርአን ወደ ምድር የወረደበት፣ የጀሃነም በሮች ተዘግተው የጀነት በሮች የተከፈቱበት፣ አማኙ እንደ እምነቱ ጽናትና እንደ አላህ (ሱወ) እዝነት ምናዳዎችን የሚያገኝበት የተቀደሰ ወር ነው።

በቁርአን አማኙ ከፈጣሪው ጋር ተነጋግሯል፤ የሚበጀውን የሕይወት መንገድ መርጦ እንደ ፈጣሪው ትእዛዝ ለመኖር ዕድል አግኝቷል። በስግደት፣ በጸሎት፣ በደግ ሥራና በእዝነት ወደ ፈጣሪ ቀርቦ በጥሞና የሚያስብበት፣ ሁሉም ራሱን የሚመዝንበት የተባረከ ወቅት ነው – ረመዳን። በዚህ ምክንያት የረመዳን ወር ሲጠናቀቅ ሕዝበ ሙስሊሙ ወሩ አለቀልን ከማለት ይልቅ አለቀብን ማለትን ያስቀድማል። ይኽ ቅዱስ ወር በሕይወቱ ውስጥ ዳግም የሚመጣበትን አጋጣሚ እየናፈቀም ይቆያል። ለዚያም ነው የረመዳን ወር በሕዝበ ሙስሊሙ ዘንድ እጅግ ታላቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ወሮች መካከል ቀዳሚው የሆነው። የረመዳን ጾም ደምቆ እንደተጀመረ ሁሉ በድምቀት አልቆ እነሆ ለዒድ አል ፈጥር በዓል ደርሰናል። ሁላችንንም እንኳን አደረሰን!

የዘንድሮው ረመዳን በኢትዮጵያ ፍቅርና ሀገራዊ አንድነት የታየበት ሆኖ በማለፉ ከመቼም ጊዜ የተለየ ተደርጎ በታሪክ ሲታወስ ይኖራል። “ከዒድ እስከ ዒድ” የተሰኘው ሀገራዊ ንቅናቄ ብዙዎችን ከመላው ዓለም አሰባስቦ በእናታቸው ቤት፣ በወገናቸው መሐል እንዲያሳልፉ ዕድል ፈጥሯል። ከመዲና ከተማችን ጀምሮ በክልል ከተሞችና በየቀየው በተዘጋጁ የጎዳና ላይ የኢፍጣር ፕሮግራሞች ወንዱ – ሴቱ፣ ሙስሊሙ – ክርስቲያኑ፣ ትንሹ – ትልቁ ኅብረትና አንድነቱን አሳይቷል። ኢትዮጵያም በልጆቿ ወንድማማችነት ደስ ተሰኝታለች።

ፈጣሪም የሚፈልገው ይኼንን ነው። በቅዱስ ቁርአኑ ላይ በግልጽ እንደሰፈረው “ልቦቻችሁን የሰበሩ ጠላቶቻችሁ ቢሆኑም እንኳ በአላህ ፈቃድ ወንድም ሊሆኑዋችሁ ይችላሉ›› በማለት ሁሉም የአደም ልጆች በአንድነት ሳይከፋፈሉ እንዲያምኑ፣ ፈጣሪ ያደረገላቸውንም እንዲያስታውሱ፣ በሰው ልጆች መሐል ፍቅርና መረዳዳት እንደሚያስፈልግ አበክሮ ይገልጻል። የቱንም ያህል የሐሳብ ልዩነት ቢኖረን፣ በባህልና በወግ – በቋንቋና በልማድ ብንለያይ፣ ያለን አንድ ሀገር እስከሆነ ድረስ፣ እነዚህ ልዩነቶችን ተሻግረን ወንድማማችና እኅትማማች እንድንሆን፣ እርስ በእርስ እንድንተሳሰብ የፈጣሪ ትእዛዝ ያሳስባል። ‹የአላህ እጅ ሰብሰብ ብለው በአንድነት በቆሙ ሰዎች መካከል ይገኛል› የሚለው የእምነቱ አስተምህሮም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።

ውድ ወገኖቼ፣

በትንሽ በትልቁ እልህና ጠበኝነትን የሚቆሰቁሱ የሸይጣን እጆች በበዙበት በዚህ ወቅት ከሁላችንም የሚጠበቀው ትዕግሥትና ሰከን ብሎ ነገሮችን በጥሞና መመርመር ነው። የነብዩ መሐመድ (ሰዐወ) ሕይወት አበክሮ እንደሚያስገነዝበን የተመኙትን ለመጨበጥ፣ ከምንም ነገር በላይ ረጋ ብሎ ማሰብን ይጠይቃል። ማሰላሰል እና ትዕግሥት ይጠይቃል። በሐዲሳቸው ላይ እንደተጠቀሰው፣ ጥድፊያ እና ችኮላ ከሸይጣን ሲሆኑ፣ ማሰላሰል እና ትዕግሥት የአላህ ናቸው ብለዋል። በቁርአንም ላይ “አላህ (ሱወ) ታጋሾችን ይወዳል” ተብሎ ተጽፏል። ነቢዩም በሌላ ሐዲሳቸው “ማንም ቢሆን፣ ከትዕግሥት የበለጠና የተሻለ በረከት ሊያገኝ አይችልም” ማለታቸው ተጠቅሷል። የታገሠ ሰው፣ ሥነ ሥርዓት ይኖረዋል። ራሱን ለመመዘንና ሌሎችን ለማየት ጥሞና ይኖረዋል። ነቢዩ መሐመድ (ሰዐወ) ለአንድ ሰዓት ያክል፣ ራስን በጥሞና ማየትና መመዘን 70 ዓመት ከመጸለይ የበለጠ ዋጋ እንዳለው ለተከታዮቻቸው አስተምረዋል። እኛም እንደ ሕዝብ ለውዲቷ ሀገራችን በጥሞና እንድንጸልይ፣ በሚዛናዊ ምልከታ እንድንራመድ፣ ለመልካምነትና ደግነት ራሳችንን እንድናስገዛ፣ የሸይጣን እጆችን በትዕግስትና በማስተዋል በትር እንድንረታ አበክሬ እጠይቃለሁ።

ሀገርን መገንባት እጅግ ብርቱ ድካም የሚጠይቅ መሆኑን ሁላችን እንረዳዋለን። በዐረብኛ ‹ከፍ ያለ ቦታ መድረስ የሚፈልግ ቢኖር ብዙ ሺህ ሌሊቶችን ሳይተኛ ማሳለፍ አለበት› የሚል ወርቃማ አባባል አለ። እኛም ከሌሎች አልባሌ ነገሮች ራሳችንን ቆጥበን፣ ዕውቀትና ጉልበታችንን ከፍ ያለ ቦታ ለመድረስ እናውለው። ኢትዮጵያ፣ ገና አሁን ከጦርነት የወጣች ሀገር ናት። ከዚያ በፊት አንበጣና ኮሮና ጫና አሳርፎብን ነበር። እሱም ሳይበቃ ድርቅ ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ ወገናችንን ክፉኛ ጎድቶታል። ብዙ ያጣነው ነገር አለና ስለጎደለብን መታገሥና በርትተን መሥራት እንጂ ተስፋ መቁረጥ የለብንም። መንግሥት የሚችለውን ሁሉ ያደረጋል። እናንተም ለሀገር ህልውና ሲሉ የተሠዉ ጀግኖችን ወደ ሕይወት መመለስ ባትችሉ በሕይወት ያሉትን መርዳት፣ ቤተሰባቸውን መደገፍ ይገባችኋል። ስለ መረዳዳት ለሕዝበ ሙስሊሙ ማስረዳት ለቀባሪው እንደ ማርዳት ተደርጎ እንደሚቆጠር ዐውቃለሁ። እናም ሰውን ከሰው ሳትለዩ፣ እከሌ ሙስሊም ነው ክርስቲያን ነው ሳትሉ፣ ከዚህና ከዚያ ወገን ብላችሁ አንዱን ከሌላው ሳትለዩ ዐቅማችሁ የፈቀደውን በማድረግ ለተጎዱ ወገኖቻችን እንድትደርሱላቸው በትኅትና እጠይቃችኋለሁ።

በድርቁም ሆነ በግጭቶች የተሰደዱትን ወገኖቻችንን ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ እናግዛቸው። ከሥራቸው ለተፈናቀሉ ሥራ እንፍጠርላቸው። ቤት ለወደመባቸው ቤት እንሥራላቸው። ከብቶቻቸው የሞቱባቸውን አርብቶና አርሶ አደሮች እንደ ዐቅማችን እናግዛቸው። እምነት ሳይለያየን ሁላችንም ተባብረን የወደቀ ወገናችንን በማንሣት ለሀገርና ለሕዝብ ያለንን ፍቅር ለዓለም እናሳይ። ጠብን በፍቅር ስናሸንፍ፣ ከወደቅንበት ተጋግዘን ለመነሳት ስንጣጣር፣ እንደ አገር አስበን ስናደርግ ሰውም ፈጣሪም ደስ ይሰኛል። ከዒድ እስከ ዒድ፣ ሁላችንንም የሚመለከት የህዝብ በዓል፣ የሀገር በዓል ይሆንልናል። የዚህ በዓል በደመቀ ሁኔታ መከበር፣ የሁላችንም ድምቀት፣ የሁላችንም ክብር እንደሆነ ማወቅ ይገባናል።

በድጋሚ፣ እንኳን ለታላቁ የዒድ አል ፈጥር በዓል አደረሳችሁ፣ አደረሰን!!

ዒድ ሙባረክ!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ሚያዚያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም.

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.