Fana: At a Speed of Life!

የስልጤ ዞን ጉዳት የደረሰባቸውን የሃይማኖትና የንግድ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የስልጤ ዞን ከሰሞኑን ጉዳት የደረሰባቸውን የሃይማኖትና የንግድ ተቋማትን በጋራ መልሶ ለመገንባት እየሰራ እንደሆነ አስታውቋል።

1ሺህ 443ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ እየተከበረ ይገኛል።

የስልጤ ዞን እስልምና ጉዳዮች ፕሬዚዳንት ሼይህ መሀመድ ከሊል በዚህ ወቅት እንዳሉት የእምነቱ ተከታዮች በጾም ወቅት ያሳዩትን የመረዳዳት ባህል አሁን በበዓሉም እንዲደግሙት ጠይቀዋል።

ሼህ መሀመድ አያይዘውም ከሰሞኑን በዞኑ የፈጠረውን ግጭት የሚወገዝ እና ድርጊቱ የስልጤን ህዝብ የማይወክል የእምነቱ አስተምህሮንም የሚጻረር ነው ብለዋል።

በቀጣይም ጉዳት የደረሰባቸውን የእምነት እና የንግድ ተቋማት መልሶ ለመገንባት ሙስሊሙ ማህበረሰብ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር በበኩላቸው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ ከሰሞኑን በዞኑ የተፈጠረው ችግር የስልጤን ማህበረሰብ የማይወክል ነው ብለዋል።

የስልጤ ህዝብ ለዘመናት ተቻችሎ የመኖር እሴት ያለው ነው፤ ይህንንም በተግባር የተጎዱ የሃይማኖትና የንግድ ተቋማትን መልሶ በመገንባት ያሳያል ብለዋል።

የዞኑ አስተዳደር እና የሃይማኖት አባቶች ጉዳት የደረሰባቸውን ቦታዎች የጎበኙ ሲሆን፥ በቀጣይም መልሶ ለመገንባት ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.