Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል ጅማ እና አሰላ ከተሞች ኢድ አልፈጥር ተከበረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በጅማ እና አሰላ ከተሞች የኢድ አልፈጥር በዓል በተለያዩ ስነ-ስርዓቶች ተከበረ።

የሰላት ስነስርዓት በጅማ ከተማ ስቴዲየም የተከናወነ ሲሆን ፥ በከተማው የሚገኝ ህዝበ ሙስሊም ታድሞበታል።

በጅማ ከተማ የታላቁ ሙኒር መስጂድ ኢማም ሼክ ሙሃመድ አባ ዲጋ፥ ህዝበ ሙስሊሙ የረመዳንን ወር በፆም፣ በፀሎት፣ በመደጋገፍና በፍቅር ማሳለፉን ገልፀዋል።

በመሆኑም የእምነቱ አስተምሮ እንደሚያዘው ቀጣዩን ጊዜ ከመጥፎ ነገሮች በመከልከልና በበጎ ተግባራት ላይ በመጠንከር ሊያሳልፍ ይገባል ብለዋል።

በአሉ ሲከበርም አቅመ ደካሞችንና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ማስታወስ እንደሚገባ ሼክ ሙሃመድ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የኢድ አልፈጥር በዓል በአሰላ አረንጓዴ ስታዲየም ተከብሯል።

በመርሃ ግብሩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአሰላ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ አብዱልከሪም መሃመድ፥ ፈጣሪን በመፍራት ችግረኞችን በመርዳትና ከክፉ ድርጊቶች ራስን በመጠበቅ የሃይማኖቱን እሴት መጠበቅና ማክበር ይገባል ብለዋል።

የአሰላ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛሊ ሀሹ በበኩላቸዉ ፥ በጾሙ ጊዜ ሲደረግ እንደነበረዉ ሁሉ ከዚህ በኋላም የሃይማኖቱ ተከታዮች በመራዳዳትና በመደጋገፍ ሃይማኖታዊ ግዴታቸዉን መወጣት አለባቸውም ብለዋል።

በሃይማኖት ስም የከተማውንም ሆነ የሀገርን ሰላም ለማወክ ከሚፍጨረጨሩ ጥቂት ጸረ ሰላም ሃይሎችም ራስንና ከተማዋን መጠበቅ አለብን ያሉት ከንቲባው ፥ በቀጣይነትም ለሰላም ዘብ መቆም ከሃይማኖቱ ተከታዮች እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።

የሙስሊሙ ማህበረሰብ ለሚጠይቃቸው ጥያቄዎችም በየደረጃዉ ምላሽ ለመስጠት ጥረት እንደሚደረግም ነው የተናገሩት።

በሙክታር ጠሃ ፣ አሊዪ ገመቹ እና ጀማል ገንዶ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.