1 ሺህ 443ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በሶማሌ ክልል ተከበረ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 1 ሺህ 443ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል ሶማሌ ክልል በድምቀት ተከበረ።
በበዓሉ ላይ ምዕመናን ለኢድ ሶላት ከየቤታቸው በመውጣት ሀይማኖቱ በሚያዘው መሠረት በመሰባሰብ ፍፁም ሰላም በሰፈነበት ሁኔታ በደስታ ማክበራቸው ተገልጿል።
በዓሉ በክልሉ መዲና ጅግጅጋ ከተማም በደማቅ ሥነ ስርዓት የተከበረ ሲሆን ፥ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመርሃ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት በዓሉን የምናከብረው በክልላችን ድርቅ በተከሰተበት ወቅት ነው ብለው፥ ሆኖም መንግሥት ለድርቁ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ዜጎች መታደግ ተችሏል ብለዋል።
አክለውም የኢድ አልፈጥር በዓል ስናከብር አቅመ ደካማ የሆኑ ዜጎችን በመርዳትና ያለንን በማካፈል የደስታ ተቋዳሽ ማድረግ አለብን ነው ያሉት።
የበዓሉ በሰላም መከበር የክልሉ የፀጥታ አካላትና ተቋማት ሚና ከፍተኛ እንደነበር ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።