Fana: At a Speed of Life!

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 1ሺህ 443ኛው ኢድ አልፈጥር ተከበረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ 1ሺህ 443ኛው ኢድ አልፈጥር በተለያዩ ሁነቶች ተከበረ።

በ1 ሺህ 443ኛው የኢድ አል-ፈጥር በዓል ላይ የተገኙት የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዱልሙኒየም አብዱልዋህድ እንዳሉት ፥ በከተማዋ የሚኖሩ ብሄር ብሔርሰቦችና ህዝቦች የጋራ ሰላማቸውን በማስጠበቅ የረመዳን ፆም በሰላም እንዲጠናቀቅ የጎላ ሚና አበርክተዋል ብለዋል፡፡

የሰላት ስነ ስርዓት ያለምንም የፀጥታ ችግር በደመቀ ሁኔታ እንዲካሄድ ለተሳተፉ ሰላም አስከባሪ ፀጥታ አካላት ከንቲባው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ጽንፈኛ የሀይማኖት መሪዎችና ፀረ- ሰላም ሀይሎች የሚያራምዱትን ተልዕኮ ባለመከተልና በማጋለጥ የከተማዋን ሰላም መጠበቅ እንዳለባቸው ከንቲባው አሳስበዋል፡፡

በኢድ አልፈጥር በዓል ላይ እየታየ ያለው አብሮነትና አንድነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቶ አብዱልሙኒየም ተናግረዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ከረር አልቀሪብ በወርሃ ረመዳን ለአቅም ደካማዎች ሲተገበሩ የነበሩ በጎ ስራዎች በመጪው ጊዜያትም መሰል ተግባራት እንዲከናወኑ ተናግረዋል፡፡

በኢድ አልፈጥር በዓል ላይ የታየው አንድነት ለማስቀጠል ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር በመከባባርና በመፈቃቀር የሀገርን ሰላም መጠበቅ እንደሚገባም ሼህ ከረር አልቀሪብ ጥር አቀርበዋል፡፡

የእምነቱ ተከታዮች በበኩላቸው ፥ በከተማዋ በኢድ አልፈጥር በዓል በሰላም መከበሩ የብሄር ብሔርሰቦችና ህዝቦች የመቻቻል ተምሳሌት ነው ብለዋል፡፡

የሀይማኖት መሪዎች ሀይማኖታዊ አስተምሮን በመከተል ከወገኝተኝነት በመፀዳት መዕመኑን ሊያስተምሩ እንደሚገባም የበዓሉ ታዳሚዎች ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ፅንፈኛ የሀይማኖት መሪዎችና ተከታዮች ሀይማኖትን ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋና እንድትፈረስ የሚጥሩ አካላትን መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወሰድ ማመላከታቸውን ከክልሉ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.