Fana: At a Speed of Life!

የሶማሌ ክልል መንግስት ብሄርና ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ክልሉን የብጥብጥ መናኸሪያ ለማድረግ በሚሞክሩሃይሎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠነቀቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሄርና ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ሶማሌ ክልልን የሁከትና ብጥብጥ መናኸሪያ ለማድረግ የሚሞክሩና በህጋዊ ፖለቲካ ፓርቲ ሽፋን ለውጭ አካላት የሚላላኩ ሃይሎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የሶማሌ ክልል መንግስት አስጠነቀቀ።

የክልሉ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባወጣው መግለጫ ፥ በሀገርና በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየታዩ እና እያቆጠቆጡ ያሉ አካሄዶችን በአፅንኦት ሲመለከት መቆየቱን አንስቷል።

በተለይም ፅንፈኛ በሆኑ አካላት በሃይማኖት ሽፋን ከውጭ ሃይሎች ጋር በመስራት አብሮ ተዋልዶና ተጋብቶ በኖረ ህዝብ መካከል መከፋፈልን እና ብጥብጥን ለመፍጠር እየተሰሩ ያሉ እኩይ ተግባራትን የክልሉ መንግስት እና ህዝብ አጥብቆ የሚኮንነው እና የሚያወግዘው ተግባር እንደሆነም ገልጿል።

የክልሉ መንግስት በተለይም ብሄር እና ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ክልሉን የሁከትና ብጥብጥ መናኸሪያ ለማድረግ የሚሞክሩና በህጋዊ ፖለቲካ ፓርቲ ሽፋን ለውጭ አካላት የሚላላኩ ሃይሎችን ጭምር ለይቶ በማውጣት አስፈላጊውን ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።

በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊና የክልሉ ነዋሪ ከውጭ አካላት በሚወረወር ፍርፋሪ ሀገር ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ተደርጎ ተቀባዮቻቸውን ነጥሎ በማውጣት ለህግ በማቅረብ እንዲሁም ኢትዮጵያን ለመበታተን እያደረጉት ያለውን ጥረት በንቃት በመከላከል ከመንግስት ጎን በመቆም በሃይማኖትም ሆነ በብሄር ሽፋን የሚፈፀም ሽብርተኝነትንና ፅንፈኝነትን በጋራ እንዲመክትና አምርሮ እንዲታገል ማሳሰቡን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.