Fana: At a Speed of Life!

ክልሉን የሁከትና የጦርነት ማዕከል ለማድረግ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የሐረሪ ክልል አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ህዝቡን በመከፋፈል ለማጋጨት እና ክልሉን የሁከትና የጦርነት ማዕከል ለማድረግ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የሐረሪ ክልል አስታወቀ፡፡

የሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጠው መግለጫ÷ በሐይማኖትና በብሄር ሽፋን ሕዝቦችን በማጋጨት አገር የማፍረስ ሴራ መቼም አይሳካም ሲል ገልጿል፡፡

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል

በሐይማኖትና በብሄር ሽፋን ሕዝቦችን በማጋጨት አገር የማፍረስ ሴራ መቼም አይሳካም!

የሀገራችን ታሪካዊ የውጪ ጠላቶች ሀገር ለማፍረስ ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች መካከል የሃይማኖት ፅንፈኝነት እና አክራሪነት በዋናነት ይጠቀሳሉ።

በሐይማኖትና በብሔር ሽፋን በሀረሪ ክልል ለዘመናት በሰላም፣ በፍቅር፣ በመቻቻልና በአብሮነት የኖረ እና እየኖረ የሚገኘውን ህዝብ በመከፋፈል ለማጋጨት እና ክልሉን የሁከትና የጦርነት ማዕከል ለማድረግ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል።

በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሃይማኖትንና ብሔርን ሽፋን በማድረግ እንዲሁም በሌሎች መንገዶች ሁከትና ብጥብጥን ለመፍጠር በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ የክልሉ መንግስት የጀመረውን ህግና ስርዓት የማስከበር ስራ እና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ እንቅስቃሴ አጠናክሮ ይቀጥላል።

ይህንን ተግባር ለማስፈፀምም የክልሉ መንግስት ሙሉ ቁርጠኝነትና ጠንካራ አቅም እንዳለው በዚህ አጋጣሚ መገንዘብ ያስፈልጋል።

በየደረጃው የሚገኙ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች የጥፋት ሀይሎችን ሴራ በማውገዝ የአካባቢያቸውን ሰላም እና ደህንነት ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል።

ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1443ኛው ኢድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ።
በድጋሚ ኢድ ሙባረክ!

የሀረሪ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት

ሚያዚያ 24/2014
ሐረር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.