የጠላቶቻችንን ሴራ እያፈረስን የሀገራችን ብልጽግና እውን እናደርጋለን -የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጠላቶቻችንን ሴራ እያፈረስን የሀገራችንን ብልጽግና እውን ለማድረግ እንሰራለን ሲል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ገለጸ፡፡
የክልሉ መንግስት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ሀገራችን ለረጅም አመታት ያዳበረችውን አብሮ የመኖር እሴት በሀገር ውስጥ እና የውጭ ጠላቶች ሴራ ሳትንበረከክ በብሄር ብሄረሰቦች መሀል ፍቅር፣ መከባበር ፣አብሮነት በማስፋት ከትውልድ ወደትውልድ እያሸጋገረች እስከ ዛሬ ደርሳለች ብሏል በመግለጫው።
ተከባብሮ እና ተደጋግፎ የሚኖረውን ህዝብ ለማቃቃር የተለያዩ ሴራዎች በመፍጠር የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት እንዲሸረሸር ለማድረግ ቢሞክሩም ህዝቡ እጅ ሳይሰጥ ባህሉን፣ እሴቱን እና ሃይማኖትን ጠብቆ እንደሚገኝም አስታውቋል።
የሀገሪቱ ጠላቶች ሃይማኖትን ከለላ በማድረግ በሰላም ተከባብሮ በሚኖር ህዝብ መሃል መርዝ በመርጨት የጠላቶቻችን ሴራ ለማስፈጸም ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ ያለው መግለጫው፥ መንግስትም ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማስፋት በፍቅር ተደምረው በአንድነት እንዲሻገሩ ሴራን በሚጠነስሱ ጠላቶች ላይ እርምጃ በመውሰድ እንደሚገኝም ገልጿል፡፡
የሀገራችን ጠላቶች በዛሬው ቀን የኢድ አልፈጥር በዓልን ለማክበር በወጣው ህዝብ ውስጥ በመደበቅ የውጭ አካላትን ዕኩይ አላማ ለማሳካት በአዲስ አበባ ከተማ ያደረጉት ሙከራ በሃይማኖቱ ተከታዮች እና በጸጥታ አካላት ብርቱ ጥረት እንዳልተሳካም መግለጫው ጠቅሷል ፡፡
ህዝቡ አሁንም አንድነቱን እና የአብሮ የመኖር እሴቱን በማስቀጠል ሃማኖትን እና ብሄርን ምክንያት በማድረግ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ከመንግስት ጎን እንዲቆም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጥሪ ማቅረቡን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡