መንግስት ለህዝብ ሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራ በመሆኑ ሰላምን የሚያውኩ ተግባራትን መታገስ አይችልም- አፋር ክልል
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 24 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ በመመሸግ የራሱን ድብቅ አጀንዳ ለማስፈፀም የሚሞክርን፣ ግጭቶችን በመቀስቀስ አትራፊ ለመሆን የሚደረገውን ሩጫ ህዝባችን ፈፅሞ አይታገስም ሲል የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ።
መንግስትም ለህዝብ ሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራ በመሆኑ ሰላምን የሚያውኩ ተግባራትን መታገስ አይችልም ሲል የአፋር ክልል መንግስት መግለጫ አውጥቷል።
የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።
የኢድ አል ፈጥር በዓል የሰላት ስነ-ስረአት በአፋር ክልል ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተጠናቋል።
በዛሬው ዕለት የተከበረው 1443 ሂጅራ የኢድ አል ፈጥር የሰላት ስነ ስረአት በአፋር ክልል ሰላማዊ በሆነ መልኩ የተጠናቀቀ ሲሆን ህዝቡ የተቸገሩን በመርዳት በተለይም በጁንታው ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ጋር በጋራ በመሆን ኢዱን በማሳለፍ ላይ ይገኛል።
ኢዱ ከወትሮው በተለየ መልኩ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በማሰብ አለኝታነትን በማሳየት ኢዱን በጋራ በደስታና በአብሮነት ስሜት እያሳለፉ ነው።
ህዝቡ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነተን በተግባር በማሳየት ሁሉም በየአካባቢው ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ወንድም የወንድሙ ጠባቂ መሆኑን በማስመስከር ላይ የሚገኝ ሲሆን ስለ ሰላም መስራት፣ ወደ ሰላም ጥሪ ማድረግ፣ ሰላምን መኖርን በማሳየት ላይ ይገኛል።
ሰላም ለሁሉም ነገር ዋነኛ መሰረት በመሆኑ ሁላችንም በየአካባቢያችን የሰላም ባንዲራን ልናውለበልብ ይገባል። ሰላምን ለማደፍረስ ሴራ የሚያሴሩ፣ ህዝብን ከተረጋጋ ኑሮው በማፈናቀል፣ በመግደል እና በማሳደድ ርካሽ የፖለቲካ ትርፍን ለማግኘት የሚያደርጉትን መሯሯጥ በጋራ በመሆን መግታት ግድ ይላል።
በሀገራችን በየትኛውም አካባቢ የሚከሰቱ ኢ-ፍትሀዊና ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች በማንም ይፈፀም በማንም ሊወገዝ እና ጥፋተኞች በጥፋታቸው ልክ ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል።
ይሁንና በየትኛውም ጫፍ ችግር ቢያጋጥም ችግሩን በማባባስ ሳይሆን ችግሩን አላህ በሚወደው መንገድ በሰከነ አእምሮ በቅንነት በመፍታት መረባረብ ማገዝ ይጠበቅብናል ። እሳት ላይ ቤንዝን ማርከፍከፍ ጀግንነት ባለመሆኑ ለጠላቶቻችን በር መክፈት እና የበለጠ ለአደጋ ተጋላጭ ከመሆን ያለፈ ትርፍ አያስገኝልንም።
ሰላም ከሌላ ሃይማኖትን በአግባቡ መከወን ይከብዳል፣ ሰላም ከሌለ ስለ ብልፅግና ማውራት ይከብዳል፣ ሰላም በአካባቢያችን በውስጣችን ከታጣ ሁሉ ነገር ይቃወሳል፣ በመሆኑም ውስጣችንን፣ አካባቢያችንና ሀገራችንን ብሎም አለማችንን ሰላማዊ ለማድረግ የእያንዳንዳችን ድርሻ የማይናቅ ሚና ስለሚጫወት ቅድሚያ ለሰላም መስጠት ይጠበቅብናል።
በመጨረሻም የኢድ አል ፈጥር በአል ሰላት በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸው ትልቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ባለ ድርሻ አካላት ላቅ ያለ ምስጋና እያቀረብን ሰላም የእለት ተእለት ጉርስ በመሆኑ በዘላቂነት ሰላማችንን በማስጠበቅ ህዝባችን ከጥንት ጀምሮ ያዳበረውን ለሰላም ያለውን ትኩረትና ቅድሚያ መስጠት በማጠናከር ልንቀጥል ይገባል።
የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
ሚያዝያ 24/2014
ሠመራ