Fana: At a Speed of Life!

ህዝቡ ሀይማኖትን ሽፋን ያደረገ ሁከትና ብጥብጥ ፈጣሪዎችን ለህግ በማቅረብ ከመንግስት ጎን መቆም አለበት – የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 24 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልሉ ህዝብ ሀይማኖትን ሽፋን ያደረገ ሁከትና ብጥብጥ ፈጣሪዎችን ለህግ በማቅረብ ከመንግስት ጎን መቆም እንዳለበት የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ገለጸ፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ የጸጥታ ጉዳዮች በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል፡፡

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል

ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ

ሀገራችን ኢትዮጵያ ህብረ ብሄር፣ህብረ ቋንቋ ህብረ ባህልና የተለያዩ ሀይማኖቶች መገኛ ነች። እነዚህ ሁሉ ህብረ ቀለማት የሀገራችን የኩራትና የማንነታችን መገለጫ ሁነው ለብዙ ሽህ አመታት ዘልቀዋል።

በተለያየ ጊዜ ሀገራችን ለሚገጥማትና ለሚነሱባት የውስጥና የውጭ ጠላቶቿ ብሄር፣ ቋንቋ፣ሐይማኖትና ባህል ሳይገድባቸው በተባበረ ክንድ ጠላትን እያሳፈሩ ዳር ድንበሯን በማስከበር የጀግና ህዝብ መገኛ ምድረ-ቀደምት ሀገር እንደሆነች አለም የሚያውቀው ሀቅ ነው።

አንድነት ሃይል ነው እንደሚባለው የአንድነትን ትርጉም ከኢትዮጵያኖች በላይ የሚረዳ የለም። አንድ ሁነው ጠላቶቻቸውን በመመከት ሀገራቸውን ከቅኝ ገዠወች በመጠበቅ ነፃነትን የሚቀዳጁና የሚሹ በመሆናቸው ከሀገራችን አልፎ ለአፍሪካና የአለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነትና የኩራት ተምሳሌት በመሆን አድዋ ላይ ያስመዘገቡት ድል ሁሌም ሲዘከር እንዲኖር አስችሏል።

ሰሞኑን በክልላችን ጎንደር አካባቢ የተከሰተው ሀይማኖትን ሽፋን ያደረገ ብጥብጥ አስነዋሪ ተግባርና ለዘመናት የገነባነውን የመቻቻልና የአንድነት እሴት የሸረሸረ ነው።

ክልላችን ላይ ለብዙ ሽህ አመታት ተከባብሮና ተቻችሎ በፍቅርና በአንድነት የኖሩትን የክርስትናና የእስልምና ሀይማኖቶችን በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ከውጭና ከውስጥ የተደረገ የጠላቶቻችን ሴራ እንደሆነ የክልሉ መንግስት ይገነዘባል።

ጠላቶቻችን ከውጭም ከውስጥም በሚያደራጁትና በሚያቀነባብሩት ሴራ ባንዳዎችንና ተላላኪወቻቸውን በገንዘብ በመደለል በመደበኛ ውጊያ ያልቻሉትን ሀገር የማፍረስ እኩይ አላማቸው በሐይማኖት ውስጥ እየገቡ ማባሪያ የሌለው ሁከትና ጥፋት መፈጸም ይፈልጋሉ።

የሀይማኖት ግጭት በመፍጠር አንደኛው በአንደኛው ሀይማኖት ላይ ለጥፋት እንዲነሳ በማድረግ የዜጎች ህይወት እንዲጠፋና ጉዳት እንዲደርስባቸው ቤተ-እምነቶች እንዲወድሙ ቅርሶች እንዲጠፋ፣የዜጎች ህይወት እንዲጠፋና ክልሉ የትርምስ ቀጠና ሆኖ ክልሉም ሆነ ሀገር እንዲፈርስ የተሄደበት ጽንፈኝነት በአጭሩ ካልተቀጨ አደገኛ እንደሆነ እንረዳለን።

የክልላችን ህዝብ የሚታወቅበት እሴቶቹ አንዱ የሀይማኖት መቻቻልና መከባበር ሲሆን የክርስትናና የእስልምና ሀይማኖቶች አንዱ የአንደኛውን ቤተ-እምነት ሲያሳንጽና ሲገነባ የኖረ፣ አብረው ተረዳድተው ሲሰሩ የኖሩ፣ በዓላቶቻቸው በጋራ የሚያከብሩ፣ በደስታውም ሆነ በችግር አብረው የሚቆሙ መሆኑ ለክልሉ ብቻ ሳይሆን ለሀገራችን ልዩ ልዩ ቤተ-እምነቶች ትልቅ ኩራት የሚሆኑና ትምህርት የሚወሰድባቸ ትልቁ ማንነታችን ሆኖ ሳለ ከውስጣችን በሚበቅሉ የውጭ ጠላቶቻችን ተላላኪወች ግጭት ጠማቂ በመሆን ሰላም ወዳዱን ህዝባችን እያመሡት ይገኛሉ።

በመሆኑም ሁሉም የክልላችን ህዝብ ለብዙ ሽህ አመታት የገነባነውን እሴቶቻችንና አኩሪ ባህላችን ጸንቶ እንዲዘልቅ ከውጭና ከውስጥ ጠላቶቻችን በገንዘብ ተገዝተው ሊያፈርሱን የተነሱትን ፅንፈኛ ሀይሎች ያለ ምህረት ሊታገላቸው ይገባል።

የክልላችን ህዝብ ያለምንም የሀይማኖትና የፆታ ልዩነት ሀይማኖትን ሽፋን ያደረገ ሁከትና ብጥብጥ መቋጫ የሌለው መሆኑን ተገንዝበን በተረጋጋ መንፈስና በአስተዋይነት አጥፊን በመለየትና ለህግ በማቅረብ ልንሻገረው ይገባል።

የክልላችን ወጣቶች የትኛውም ሀይማኖት ሰላምን አንድነትን ፍቅርንና መደጋገፍን እንጅ ጥላቻንና መለያየትን አይሰብክምና እርስ በእርሳችን ሊያባሉን የተነሱ የዘመናት ጠላቶቻችን በሃይማኖት ሽፋን ጽንፈኛ ሃይሎች የፈጠሩትን ገጭትና የደረሰውን ጉዳት ቆም ብሎ በማሰብ የተጎዳው ሁሉም አማራ መሆኑን ፣ የተጠቀሙት ደግሞ ፅንፈኞቹ እንደሆኑ መረዳት አለብን። ስለሆነም እነዚህ ፅንፈኞች በሚፈጥሩት ጥፋት ክልላችን ከአጀንዳ ላይ ሌላ አጀንዳ እየተቀበለ ከመደበኛ የልማት ሰራወቻችን እየወጣን ድህነትን እያባባስን ስለሆነ አሁን የተቃጣብንን አደጋ ያለምንም ልዩነት በፍፁማዊ ወንድማማችነት ወንጀለኞችን ወደ ህግ ለማቅረብ ከክልሉና ከፌዴራል የፀጥታ ሃይሎች ጎን በመሰለፍ ሴራውን ልታከሽፉ ይገባል።

ወጣቶች የሀገር ተረካቢወች ብቻ ሳትሆኑ ዋና ባለቤት በመሆናችሁ የክልሉ ሰላም በአስተማማኝ ደረጃ እንዲገነባ ለሠላም ትልቅ ዋጋ ልትሰጡ ይገባል። ስለሆነም በየትኛውም መንገድ ፅንፈኝነትንና ፅንፈኛ ሃይልን በማውገዝ ወንጀለኛን በማጋለጥ የአካባቢያችሁን የክልላችሁን ብሎም የሀገራችሁን ሰላም ልትጠብቁ ይገባል። በመሆኑም ሀሉም ወጣት ከክልሉ መንግስት ጎን በመሰለፍ ሰላማችንና አንድነታችን በሚያውኩ ፅንፈኛ ሃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ለክልላችሁ ዘብ ልትቆሙ ይገባል።

በክልላችን ውስጥ በየትኛውም መንገድ የህዝባችን ሰላምና አንድነት የሚያናጋ በሃይማኖትም ይሁን በሌላ ማናቸውም ዘዴ ግጭትን የሚሰብኩ፣ የሚቀሰቅሱ እና የጸጥታ መዋቅሩን ስራ በሚያደናቅፋ ማንኛውንም አካልና ግለሰብ ላይ የክልሉ መንግስት እየወሰደ ያለውን ርምጃ አጠናክሮ የሚያስቀጥል መሆኑን ያስገነዝባል።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት

ሚያዚያ 24/2014 ዓ.ም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.