Fana: At a Speed of Life!

የጦር መሳሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሞከሩ የአልሸባብ ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 24 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን ኤልከሬ ወረዳ ለሽብር ጥቃት ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሞከሩ የአልሸባብ ቡድን አባላት ከጦር መሳሪያ እና ጥይቶቻቸው ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አስታወቀ።

የክልሉ ልዩ ኃይል በአፍዴር ዞን ኤልከሬ ወረዳ ቡላ ቀበሌ ለሽብር እና ብጥብጥ ዓላማ ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ የነበሩ በርካታ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ እና ጥይቶችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።

በቁጥጥር ስር የዋለው በ18 ሳጥን የታሸገ 12 ሺህ 600 የክላሽንኮቭ ጥይት ፣ ስድስት አር ፒ ጂ (ባዙቃ) እንዲሁም ሁለት ብሬን (መትረየስ) መሳሪያ እና ጥይቶች መሆናቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

መሳሪያውን ይዘው ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሞከሩ የአልሸባብ ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን መሳሪያዎቹን ወደ ክልሉ በማስገባት ሁከትና ብጥብጥ የመፍጠር አላማን አንግበው እንደነበር የክልሉ ልዩ ኃይል ገልጿል።

ቀደም ባሉ ጊዜያትም የክልሉ ልዩ ኃይል በተደጋጋሚ ወደ ሀገር ውስጥ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን እና ፈንጂዎችን ይዘው ለመግባት የሞከሩ የሽብር ቡድኑ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋሉ የሚታወስ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.