Fana: At a Speed of Life!

1 ሺህ 443ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል በጋምቤላ ከተማ ተከበረ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 24 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ህዝበ ሙስሊሙ በፆም ወቅት ያሳየውን መደጋገፍና አብሮነት ከኢድ አል ፈጥር በዓል በኋላም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የጋምቤላ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አሳሰቡ።

የኢድ አል ፈጥር የሶላት ሥነ-ሥርዓት በጋምቤላ ከተማ የሃይማኖታዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም ተካሄዷል።

የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ ሲራጅ አማን በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩትን በመደገፍና አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

በተለይም በረመዳን ወቅት ያሳየውን መተሳሰብ፣ መደጋገፍ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያን ሰላም የማይፈልጉ ጽንፈኛ ቡድኖች በሃይማኖቶች ሽፋን ለዘመናት ጸንቶ የቆየውን አብሮነትና መቻቻል ለማሻከር የሸረቡት ሴራ የትኛውንም እምነት ስለማይወክል ሁሉም ሊያወግዘው ይገባል ነው ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ።

በሶላት የተሳተፉት ምዕመናን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት አባቶች ያቆዩትን ህብረትና አንድነት በማጠናከርና የሌላቸውን መደገፍ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተለይም አባቶች በአብሮነት፣ በመቻቻል ያቆይዋት ሀገር በዚህም ትውልድ ተጠብቃ እንደምትቀጥል እምነታቸውን ተናግረዋል።

የትኛውንም እምነት በማይወክሉ ጥቂት ጽንፈኛ የጥፋት ቡድኖች ክርስቲያኑንና ሙስሊሙን ለማጋጨት የተደረገው ሙከራ የሚወገዝ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.