Fana: At a Speed of Life!

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የኢንዱስትሪውን ዘርፍ መደገፍ እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የኢንዱስትሪውን ዘርፍ መደገፍ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡

የክልሉ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ፣ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና የዘርፉን ኢንቨስትመንት ለማበረታታት፣ “ኢትዮጵያ ታምርት ” በሚል መሪ ሀሳብ የንቅናቄ መድረክ በሚዛን አማን ከተማ አካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የዕድገትና ተወዳዳሪነት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡልቡልታ÷ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ራሳችንን በመቻል በኢኮኖሚ ተወዳዳሪ በመሆን ከውጭ የኢኮኖሚ ጥገኝነት መላቀቅ ይኖርብናል ብለዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው የቆዩ 60 ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲመለሱ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪ፣ የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጂዮ ሳፒ በበኩላቸው÷ በክልሉ የሚገኙትን የተፈጥሮ ሀብቶች በመጠቀም ዜጎች ውጤታማ እንዲሆኑ በዘርፍ የተሠማሩ ኢንተርፕራይዞችን ደግፎ ማብቃት ከባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ተግባር ነው ብለዋል።

አምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅማቸው እንዲጎለብት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሪት ቤቴልሄም ዳንኤል ናቸው፡፡

በክልሉ 1 ሺህ 480 እንዱስትሪዎችን ወደ 3 ሺህ ለማድረስ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.