Fana: At a Speed of Life!

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዓመታዊ ስብስባ በሴኔጋል ዳካር ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (ዩኤንኢሲኤ) 54ኛ ዓመታዊ ስብሰባውን በሴኔጋል ዳካር ይካሄዳል በቀጣዩ ሳምንት ያካሄዳል።

ስብሰባው ከግንቦት 3 እስከ 9 ቀን 2014 “የአፍሪካን መልሶ ማገገም ፋይናንስ ማድረግ ፤ በአዲስ ፈጠራ የተሻለ ውጤት ማምጣት” መሪ ቃል የሚከናወን ነው።

ስብሰባው በዋናነት የአፍሪካ አገራት የልማት ፋይናንስ ክፍተቶች በራሳቸው ሃብት መሙላት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እንደሚመክር ኢዜአ ከኮሚሽኑ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ዝቅተኛ የሃብት ማሰባሰብ አቅም፣ መንግስታት ለልማት ፕሮጀክቶች የሚበደሩት ገንዘብ እየጨመረ መምጣት እንዲሁም የእዳ ጫናና እዳ ማሸጋሸግ ላይ ያሉ ፈተናዎች የአፍሪካ የልማት ፋይናንስ መገለጫዎች እንደሆኑ ገልጿል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የፋይናንስ ፍላጎት መጨመር እና የሁለትዮሽና የባለብዙ ዘርፍ አፍሪካ ከወረርሽኙ በደረሰባት የኢኮኖሚ ጉዳት መልሳ እንድታገግም እያደረጉ ያለው ድጋፍ እየቀነሰ መምጣቱን አመልክቷል።

በተለያዩ ምክንያቶች በአፍሪካ የልማት ፋይናንስ የተፈጠሩትን ክፍተቶች ለመድፈን የአገር ውስጥ የፋይናንስ አቅምን ማጎልበትና የውጭ ፋይናንስን ውጤታማ በሆነ መልኩ መጠቀም ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው ጉዳይ እንደሆነ ነው ዩኤኢሲኤ ያስታወቀው።

አፍሪካ ለልማት ፋይናንስ የሚያስፈልጋትን ገንዘብ ከራሷ ሀብት ማሰባሰብ ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነና በዚህ ረገድም በስብሳብው የግሉ ዘርፍ የፋይናንስ ድጋፍ በሚያደርግበት ሁኔታ ላይ ምክክር እንደሚደረግ ተገልጿል።

የአፍሪካ መንግስታትን የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የሃብት ምንጫቸውን ከአገር ውስጥና የውጭ የፋይናንስ ድጋፎች ጋር እንዲያስተሳስሩ በምን መልኩ መደገፍ ይገባል? በሚለው ጉዳይ ውይይት ይደረጋል ተብሏል።

በስብሰባው ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የፈጠረውን ስጋት ወደ እድገትና ብልጽግና ለመቀየር የጀመሯቸውን ጥረቶች እንዲያጠናክሩ ጥሪ እንደሚቀርብም ተነግሯል።

54ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን(ዩኤንኢሲኤ) ዓመታዊ ስብስባ በሶስት ተከፍሎ ይካሄዳል።

ከግንቦት 3 እስከ 5 ቀን 2014 ዓ.ም የባለሙያዎች ኮሚቴ፣ግንቦት 6 እና 7 ቀን 2014 ዓ.ም የጎንዮሽ ስብስባዎች እንዲሁም ግንቦት 8 እና 9 ቀን 2014 ዓ.ም የፋይናንስና ኢኮኖሚ ሚኒስትሮች ስብሰባ ይካሄዳል።

53ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (ዩኤንኢሲኤ) እ.አ.አ በ2021 በአዲስ አበባ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.