የኬንያው ፕሬዚዳንት ምክትላቸው ከኃላፊነት እንዲነሱ መጠየቃቸውን ተከትሎ በመካከላቸው የተፈጠረው ውጥረት ተባብሷል
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ዊሊያም ሩቶ ከኃላፊነት እንዲነሱ መጠየቃቸውን ተከትሎ በመካከላቸው የተፈጠረው ውጥረት ተባብሷል፡፡
ውጥረቱ የተባባሰው ፕሬዚዳንት ኬንያታ÷ በሀገራቸው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ ወሳኝ እርምጃዎችን አልወሰዱም በማለት ምክትላቸውን ከስልጣን እንዲነሱ መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው፡፡
ወቀሳውን ተከትሎ የኬንያ ምክትል ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በትዊተር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ የኬንያ መንግስት የካቢኔ ስብሰባ የተዘጋጀው ከ 2 ዓመት በፊት እንደነበር ጠቁመው ፕሬዚዳንት ኬንያታም ኃላፊነታቸውን እንዳልተወጡ ገልፀዋል፡፡
በኬንያ በነሃሴ ወር ላይ አጠቃላይ ምርጫ ለማድረግ 47 እጩዎች ውድድሩን የተቀላቀሉ ሲሆን÷ በኬንያ ሕገ መንግስት መሰረት ፕሬዚዳንት ኬንያታ ከሁለት ዙር ምርጫ በኋላ በድጋሜ መወዳደር አይችሉም፡፡
ምክትል ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ከእርሳቸው ይልቅ ለቀድሞው የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ ድጋፍ ማሳየታቸው ከፕሬዚዳንት ኬንያታ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አሻክሯል ነው የተባለው፡፡
ባለፈው አርብ የቀድሞው መሪ ሙዋይ ኪባኪ ቀብር ላይ የተገናኙት ፕሬዚዳንቱ እና ምክትላቸው እጅ ለእጅ አለመጨባበጣቸው ውጥረቱ መባባሱን እንዳሳየ አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በኬንያ የምርጫ ውድድር የዋጋ ንረት ዋነኛ ጉዳይ ሲሆን÷ ፕሬዚዳንት ኬንያታ ባለፈው እሁድ የኬንያን ዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ 12 በመቶ ጭማሪ እንዲደረግ መወሰናቸው ይታወሳል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡