Fana: At a Speed of Life!

በቀድሞ የመከላከያ መኮንኖች የክስ መዝገብ ላይ 1ኛ ተከሳሽ ሕይወት ማለፍን ተከትሎ በሌሎች ተከሳሾች ላይ የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀድሞ የመከላከያ መኮንኖች የክስ መዝገብ ላይ 1ኛ ተከሳሽ ሜጀር ጀኔራል ገብረመድህን ፍቃዴ(ወዲ ነጮ) ድንገተኛ ሕይወት ማለፍን ተከትሎ በሌሎች ተከሳሾች ላይ የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱ ተገለፀ ።

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ ሽብርና የህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ለዛሬ ተይዞ በነበረው ተለዋጭ ቀጠሮ ቀሪ የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ተሰይሞ ቀሪ 7ኛ እና 15ኛ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ቃላቸውን ለመስጠት ተገኝተው ቃለ መሀላ ፈፅመው ነበር ።

ሆኖም ግን የፌደራል ማረሚያ ቤት የ1ኛ ተከሳሽ ሕይወት ሚያዝያ 24 ቀን 2014 ዓ.ም ድንገት ማለፉን ለፍርድ ቤት በፃፈው ደብዳቤ አሳውቋል።

በቀድሞ የመከላከያ ሚኒስቴር 1ኛ ተከሳሽ የመከላከያ የኮሚኒኬሽንና ኤሌክትሮኒክስ ሳይበር መምሪያ ኃላፊ ሆኖ ሲሰራ ከሌሎች የስራ ባልደረቦቹና ተከሳሾች ጋር በመሆን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ የሬዲዮ ግንኙነትን በማቋረጥ እና የሬዲዮ መሳሪያ ለህውሐት ወታደራዊ ቡድን አሳልፈው ሰጥተዋል ተብለው በዐቃቤ ህግ የቀረበባቸውን ክስ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሆኖ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ ሽብርና የህገመንግስታዊ ጉዳይ ወንጀል ችሎት እየቀረበ ጉዳዩን እየተከታተለ ይገኝ ነበር ።

የ1ኛ ተከሳሽ ድንገተኛ ሕይወት ማለፉን ተከትሎም በክስ መዝገቡ የተካተቱ ሌሎች ተከሳሾችና የተከሳሽ ጠበቃ የሟች አስከሬን ባልተቀበረበት ሁኔታ ዐቃቤ ህግ የሚያሰማብንን ምስክሮች ለመከላከል የሚያስችል የስነ ልቦና ዝግጅት ስለሌለን ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን ከሟች ጋርም የቆየ የስራ ባልደረባነትና ወዳጅነት የነበረን በመሆኑ አጃቢ ተመድቦልን በቀበር ስነስርዓቱ ላይ እንድንገኝ ለማረሚያ ቤት ደብዳቤ ይፃፍልን ሲሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል ።

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ በ1ኛ ተከሳሽ ድንገተኛ ሞት የተሰማውን ሐዘን ገልፆ፥ ተለዋጭ ቀጠሮውን እንደማይቃወም በማስታወቅ ተከሳሾች በአጃቢ ሆነው የባልደረባቸው የቀብር ስነስርዓት ላይ መገኘቱ ግን ስላልተለመደና ለደህንነት አስጊ መሆኑን በመግለፅ ማረሚያ ቤትም ጉዳዩን ቢመለከተው መልካም ነው ሲል ማሳወቁን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ።

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ ሽብርና የህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በፅህፈት ቤት ከተወያየ በኋላ ተከሳሾች በ1ኛ ተከሳሽ የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ለመገኘት ፍላጎታቸውን በፅሑፍ ያቅርቡና በፅህፈት ቤት ትዕዛዝ የሚሰጥበት ይሆናል ሲል 1ኛ ተከሳሽ ድንገተኛ ሕይወት ማለፉን ተከትሎ በወንጀል ህግ 214 መሰረት ክሱ መቋረጡንና በሌሎች ተከሳሾች ላይ ቀሪ የዐቃቤ ህግ ምስከሮችን ለመስማት ከግንቦት 8 እስከ ግንቦት 12 ቀን 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.