Fana: At a Speed of Life!

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲዳማ ክልል ምክር ቤት 6 ዙር አንደኛ የስራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ ምክር ቤቱ 875 ሚሊየን ብር ተጨማሪ በጀት ያጸደቀ ሲሆን ፥ ቃለ ጉባኤ ማፅደቅና አዳዲስ ሹመቶችን ያከናወናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እንዲሁም የክልሉ የዘጠኝ ወር የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት የሚደረግበት ሲሆን÷ በታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ ቀጣይ አቅጣጫ ይቀመጣል ነው የተባለው፡፡

 

በውይይቱ ላይ ሀገራዊ ምክክር እና የሀገራት ተሞክሮን የሚያሳዩ ሰነዶች ቀርበው በተሳታፊዎች ወይይት እየተደረገባቸው ይገኛል።

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ፥ የምክር ቤት አባላት የህዝብን ፍላጎት ለማሳካት የቁጥጥርና የክትትል ስራን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የምክር ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ዶራሞ፥ ባለፋት ቀናት የምክር ቤቱ አባላት የውይይትና የስልጠና ይዘት ያለው መድረክ ማካሄዱን ገልፀው አዳዲስ አባላትንም ግንዛቤ ለማስጨበጥ ትልቅ አቅም የነበረው መድረክ እንደነበረ አውስተዋል።

በመድረኩ የምክር ቤቱ ሚና፣ ለህዝብ ያለውን ወገንተኝነት፣ መብትና ግዴታዎች በምን መልኩ የቁጥጥር ስራዎችን መስራት እንዳለበት፣ ብልሹ አሰራሮችን እንዴት መታገል እንዳለባቸውና በሌሎች ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ገለፃና ውይይት መደረጉ ተገልጿል፡፡

በብርሃኑ በጋሻው እና በታመነ አረጋ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.