የሀገር ውስጥ ዜና

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ

By Feven Bishaw

May 04, 2022

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲዳማ ክልል ምክር ቤት 6 ዙር አንደኛ የስራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ ምክር ቤቱ 875 ሚሊየን ብር ተጨማሪ በጀት ያጸደቀ ሲሆን ፥ ቃለ ጉባኤ ማፅደቅና አዳዲስ ሹመቶችን ያከናወናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በውይይቱ ላይ ሀገራዊ ምክክር እና የሀገራት ተሞክሮን የሚያሳዩ ሰነዶች ቀርበው በተሳታፊዎች ወይይት እየተደረገባቸው ይገኛል።

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ፥ የምክር ቤት አባላት የህዝብን ፍላጎት ለማሳካት የቁጥጥርና የክትትል ስራን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የምክር ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ዶራሞ፥ ባለፋት ቀናት የምክር ቤቱ አባላት የውይይትና የስልጠና ይዘት ያለው መድረክ ማካሄዱን ገልፀው አዳዲስ አባላትንም ግንዛቤ ለማስጨበጥ ትልቅ አቅም የነበረው መድረክ እንደነበረ አውስተዋል።

በመድረኩ የምክር ቤቱ ሚና፣ ለህዝብ ያለውን ወገንተኝነት፣ መብትና ግዴታዎች በምን መልኩ የቁጥጥር ስራዎችን መስራት እንዳለበት፣ ብልሹ አሰራሮችን እንዴት መታገል እንዳለባቸውና በሌሎች ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ገለፃና ውይይት መደረጉ ተገልጿል፡፡