የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ በኢንተርፕራይዞች ልማት ፖሊሲ እና ስትራቴጂዎች ላይ ከኮርያ ልምድ የመቅሰም እቅድ አላት – ዶክተር ፍጹም አሰፋ

By Meseret Awoke

May 04, 2022

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ በኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ከኮርያ አምባሳደር ካንግ ሶኪ ጋር ተወያዩ ፡፡

ሚኒስትሯ ከአምባሳደሩ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ እና ኮርያ ለዘመናት የዘለቀ የልማት ትብብር እንዳላቸው ያመለከቱ ሲሆን ፥ አገራቱ በእነዚህ የትብብር ዓመታት በርካት ስኬቶችን በጋራ ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡

ኮርያ ለኢትዮጵያ ድጋፍ ያደረገችባቸውን ዘርፎች የጠቀሱት ዶክተር ፍጹም፥ ድጋፎቹ ቴክኒካዊ እና ሰብአዊ አገልግሎቶችን ያካተቱ እንደነበርም ነው የዘረዘሩት፡፡

አያይዘውም በቀደመው ጊዜ በነበረው የኢትዮጵያ እና ኮርያ ትብብር፣ ኢትዮጵያ እና ሕዝቧ በርካታ መልካም ነገሮችን መቅሰማቸውን ገልጸው፥ ይህን ግንኙነት በቀጣይ ዓመታት ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመታት ከኮርያ ጋር በሚኖራት ትብብር በተለይ በሰው ኃይል ልማት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በኢንዱስትሪ ባህል፣ ተቋማዊ ልማት፣ በማስረጃ ላይ በተመሠረተ የፖሊሲ ንድፍ እና ሌሎችም ላይ እንደምታተኩር ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ኮርያ በስኬት ከምትነሳበት በኢንተርፕራይዞች ልማት ፖሊሲ እና ስትራቴጂዎች ላይ ልምድ የመቅሰም እቅድ እንዳላት አስታውቀዋል።

ሚኒስትሯ በመጨረሻ ኢትዮጵያ እየተገበረችው ለምትገኘው የአስር ዓመቱ የልማት እቅድ ትግበራ እና ክትትል እንዲያግዛት ከኮርያ ጋር የመተባበር ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኮርያ አምባሳደር ካንግ ሶኪ በበኩላቸው ፥ አገራቸው እንደ ባለፉት ዓመታት ሁሉ ከኢትዮጵያ ጋር ለመተባበር ዝግጁ መሆኗን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡