Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ፈተናዎች በሰላማዊ መንገድ እንድትፈታ አሜሪካ ማንኛውንም ድጋፍ ታቀርባለች- አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ፈተናዎች በሰላማዊ መንገድ እንድትፈታ አሜሪካ ማንኛውንም ድጋፍ ታቀርባለች ሲሉ በኢትዮጵያ የአሜሪካ መንግስት ጉዳይ ፈፃሚ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን ተናገሩ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በኢትዮጵያ የአሜሪካን መንግስት ጉዳይ ፈፃሚ ከሆኑት አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን ጋር ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም÷ አምባሳደር ሬድዋን በትግራይ የተፈጠረውን ሁኔታና የህወሓት ቡድን ያከናወናቸውን የጥፋት ተግባር በዝርዝር አስረድተዋል።

በክልሉ የነበረው ጦርነት ያስከተለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመፍታትና ሁኔታዎችንም በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጩ ለማድረግ መንግስት ያቀረበቸውን የሰላም አማራጮች እና በወቅቱ ተደራሽ ያደረጋቸውን ሰብዓዊ ድጋፎች በሚመለከትም አምባሳደር ሬድዋን አብራርተዋል፡፡

ህወሓት መንግስት ለትግራይ ሕዝብ በማሰብ የሰጠውን የሰላም አማራጮች ሳይጠቀምበት መቅረቱን ገልጸው፥ ይልቁንም ግጭቱን ወደ አፋርና አማራ ክልሎች በማስፋፋቱ ተጨማሪ ጉዳት ማድረሱን ነው ያመለከቱት። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ህወሓት የፈፀማቸውን ወንጀሎች ለአምባሳደር ጃኮብሰን ገልፀውላቸዋል።

አሁናዊ የሰብዓዊ ድጋፍን በሚመለከትም መንግስት በትግራይ ለሚኖሩ ዜጎች የምግብና የመድሃኒት አቅርቦት በተገቢው መልኩ እንዲደርስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸው÷ ከአሁን በኋላም ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግስት ያለውን ፅኑ ፍላጎት አስረድተዋል፡፡

የህወሓት ኃይል ከአንዳንድ የአፋር ክልል እየወጣ ቢሆንም÷ አሁንም ግን ጨርሶ አካባቢውን እንዳለቀቀ አምባሳደር ሬድዋን ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ተፈፅሟል ስለተባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትም፥ መንግስት ጉዳዩን በቅድሚያ በራሱ ቀጥሎም ከተመድ በጋራ አጣሪ ቡድን ምርመራ በማድረግ በዚህ ጉዳይ ላይ ተሳትፎ አድርገዋል የተባሉ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ መስራቱን አንስተዋል።

አለማቀፉ ማህበረሰብ ግን ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች የፈፀማቸውን አሰቃቂ ወንጀሎች በመሸፋፈን አድሎዓዊ አካሂድ ሲከተል እንደነበረ ለአምባሳደሯ ማስረዳታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያ ከማንኛውም አካል ጋር በሰላምና በትብብር የመስራት ፅኑ አቋም እንዳላት የገለፁት አምባሳደር ሬድዋን÷ ለኢትዮጵያም ይሄን የሚመጥን ምላሽ ሌላ ወገን ማሳየት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

አምባሳደር ትሬሲ ጃኮብሰን በበኩላቸው ለተደረገላቸው ማብራሪያ አድናቆታቸውን ገልጸው፥ ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ፈተናዎች በሰላማዊ መንገድ እንድትፈታ አሜሪካ ማንኛውንም ድጋፍ ታቀርባለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ እና አሜሪካ ግንኙነት ዳግም ወደተሻለ ደረጃ እያደገ መምጣቱንና ግንኙነቱ ወደነበረበት እንዲመለስ እንደሚሰሩ የተናገሩት አምባሳደሯ÷ የሰብዓዊ ድጋፎች ተጠናክረው በሚቀጥሉባቸው ሁኔታዎች ላይ አሜሪካ ብርቱ ስራ እንደምትሰራም አረጋግጠዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.