የሀገር ውስጥ ዜና

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ ተጨማሪ በጀትና ዳኞችን ሹመት በማጽደቅ ተጠናቀቀ

By Meseret Awoke

May 04, 2022

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ ተጨማሪ በጀትና ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ለወረዳ ፍርድ ቤቶች የ19 ዳኞችን ሹመት በማፅደቅ ተጠናቀቀ።

የልሉ ምክር ቤት 874 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት በሙሉ ድምፅ ያፀደቀ ሲሆን፥ በጀቱ የውስጥ ገቢን በማሻሻል የሚመነጭ መሆኑ ተገልጿል። የክልሉ ም/ቤት በዛሬው ዕለት ባከናወነው 6ኛ ዙር 1ኛ የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ የክልሉ መንግሥት አስፈፃሚ አካላት የ9 ወራት ሪፖርት በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ቀርቦ የምክር ቤት አባላት ሃሳብ፣ አስተያየቶችን እንዲሁም ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡ የተነሱ ጉዳዮችን መሰረት በማድረግ ሰፊ ማብራሪያ እና ምላሾች ከተሰጡ በኋላ ምክር ቤቱ ሪፖርቱን በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።

በበጀት እና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ አማካይነት ለክልሉ ምክር ቤት የበጀት ዕቅድ ማሻሻያ ቀርቦም ተጨማሪ በጀት ያጸደቀ መሆኑን ከክልሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ምክር ቤቱ በመጨረሻም በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ደምሴ ዱላቻ አማካይነት ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ለወረዳ ፍርድ ቤቶች የ19 ዳኞችን የሹመት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፥ በቀረቡ ዳኞች ላይ የክልሉ ምክር ቤት አባላት ውይይት በማድረግ የዳኞቹ ሹመት ፀድቋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡