Fana: At a Speed of Life!

ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ የጥፋት ድርጊት ለመፈፀም ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ 145 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎንደር የተከሰተውን ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ የጥፋት ድርጊት ለመድገም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 145 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዳማ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተኮረ ከ2 ሺህ በላይ ወጣቶች የተሳተፉበት የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሄዷል።

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ ለኢዜአ እንደገለጹት ፥ የግል የፖለቲካ ዓላማቸውን ማዕከል በማድረግ በሃይማኖት ሽፋን ሀገራዊ ትርምስ ለመፍጠር እየሰሩ ያሉ አካላትን ሴራ ማክሸፍ ከወጣቱ የሚጠበቅ ቀዳሚ ተግባር ነው።

በጎንደርና ሌሎች አካባቢዎች የተከሰተውን ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ እኩይ ተግባር አዳማ ከተማ ለማምጣት ብዙ ጥረቶች መደረጋቸውን የጠቀሱት ከንቲባው ፥ በጉዳዩ ዙሪያ ከሁሉም የሃይማኖት ተቋማት አባቶች ጋር ውይይት መደረጉን አስረድተዋል።

ድርጊቱን ከማውገዝ ባሻገር ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ ስርዓት ማስያዝ መቻሉንም ነው ከንቲባው የተናገሩት።

ፅንፈኛ ኃይሎች ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ በጎንደር የፈፀሙትን የጥፋት ድርጊት ለማስፋትና ትርምስ ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 145 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ነው ያስተወቁት።

በተጨማሪም ዘጠኝ የአሸባሪው ሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁመው ፥ ህዝቡን በብልሹ አሰራርና ሌብነት ያስመረሩ 69 አመራሮች ላይ ደግሞ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን ከንቲባው አክለው ተናግረዋል።

የመድረኩ ዓላማ ወጣቶች የፅንፈኞችን የጥፋት ተልዕኮ ተረድተው የጥፋት ኃይሎችን በማጋለጥ ሂደት ውስጥ የድርሻቸውን እንዲጫወቱ ለማስቻል መሆኑን አብራርተዋል።

በየደረጃው ያለው የወጣቶች አደረጃጀት በነቃ መንፈስ የአፍራሽ ኃይሎችን ሴራ በማጋለጥ የአካባቢያቸውንና የከተማዋን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲጠብቁ ማስቻል ሌላው የመድረኩ ዓላማ መሆኑንም አመልክተዋል።

በጽንፈኞችና በአክራሪዎች ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ እየተሰሩ ያሉ ተግባራትን በማጋለጥና በማክሸፍ በከተማዋም ሆነ በክልሉ ቦታ እንዳይኖራቸው ለማስቻል መድረኩ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑንም ነው ከንቲባ ሃይሉ ጀልዴ ያስረዱት።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.