Fana: At a Speed of Life!

ሀገሪቱ በከባድ የዲፕሎማሲ ጫና ውስጥ በነበረችበት ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያሳየው የእቅድ አፈጻጸም አበረታች ነው – ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰለም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገምግሟል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶ/ር ዲማ ነገዎ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት የተካሄደው ግምገማ፥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አገራዊ ለውጥን ታሳቢ ያደረገ የለውጥ እና የሪፎርም ስራዎች በተሳካ ሁኔታ የተካሄደ መሆኑን በሪፖርት ቀርቧል፡፡

የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር ፣ ተደማጭነታችንና ተደራሽነታችን በሚጨምር መልኩ በዋና መስሪያ ቤት እና በሚሲዮኖች የአደረጃጀት ለውጥ የተደረገ መሆኑን ተብራርቷል፡፡

የተደረገው ለውጥ በዋናነት ወጪ ቆጣቢ እና ብቃት ያለውን የሰው ኃይል ስምሪት ትኩረት ያደረገ መሆኑ ነው የተገለፀው።

በተያያዘም ለተገልጋዮች በቴክኖሎጂ የተደገፉ እና ቀልጣፋ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑ የተነሳ ሲሆን፥ በዚህም በኩል የዜጎች ዕርካታ የጨመረ መሆኑን የቋም ኮሚቴ አባላት የታዘቡ መሆናቸውን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በሀገሪቱ ላይ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ በርካታ ጫናዎች እና ከበባዎች የተደቀኑ ቢሆንም በከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት ፣ በዳያስፖራው ተሳትፎ ፣ በወዳጅ አገሮች ድጋፍ ሊመጣ የነበረውን አሉታዊ ውጤት ማስቀረት መቻሉን በስኬት ተጠቅሷል፡፡

በዚህ ዙሪያ ሀገሪቱ ላይ ያተኮሩ በርካታ አጀንዳዎች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በአውሮፓ ህብረት ቢቀርቡም የውሳኔ ሀሳባቸው ማዕቀብ እንዳይጥሉ ማድረግ መቻሉ ለአብነት ተነስቷል ፡፡

በተመሳሳይም የህዳሴ ግድብ ድርድር በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር እንዲሆን ማድረግ መቻሉ በተጨማሪ ተነስቷል፡፡

ለዜጎች ቅድሚያ በሚሰጥ መልኩ እየተካሄደ ያለው የድፕሎማሲ ተግባር፣ በችግር ላይ ያሉ ወገኖች ወደ አገራቸው እንዲገቡ በማድረግ እየተደረገ ያለውም በጥንካሬ ተጠቅሷል፡፡

የዳያስፖራ አባላት በሀገሪቱ ላይ የተደረጉ ጫናዎችን በመቃወም በሰላማዊ ሰልፍ ፣ ጫና የሚፈጥሩ ግለሰቦችንና ተቋማት በማነጋገር ፣ በጦርነት የተጎዱ ወገኖች በመደገፍ፣ በአገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ገንዘብ በማዋጣት፣ በኢንቨስትመንት በመሳተፍ ፣ሬሚታንስ በመላክ እና የዳያስፖራ አካውንት በመክፈት የላቀ ሚና መጫወቱንም በስፋት ተጠቅሷል፡፡

ዳያስፖራው ታላቁ ወደ አገር ቤት ጉዞ ላይ በመሳተፍ ለአገሩ ያለውን አገርነት በተግባር ማሳየቱን በበጎ ጎኑ ተነስቷል፡፡

የአገር ገጽታ ግንባታ ሥራዎች እና የዲጅታል ዲፕሎማሲ ዜጎችን በማሳተፍ የተሻሉ ስራዎች መሰራታቸውን በግምገማው ተነስቷል፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን ከቋም ኮሚቴ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፥ ዲፕሎማሲው ስኬታማ የሚሆነው በዋናነት በሀገር ውስጥ በሚኖር ሰላም፣ አንድነትእና የኢኮኖሚ ልማት ጋር የተያያዙ ጥንካሬዎች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዲፕሎማሲ ሥራ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰራተኞች ብቻ የማይከናወን በመሆኑ የሁሉንም ዜጋ የበኩሉን ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅሰው፥ በቀጣይም በሀገሪቱ ላይ በተለያዩ መልኩ የተከፈቱትን ጫና ለመቋቋም የማስገንዘብ እና የማለዘብ ሥራዎችን ለመሥራት አዲስ ስትራቴክ ዕቅድ መዘጋጀቱንም አስረድተዋል፡፡

የቋም ኮሚቴ ሰብሳብ ዶ/ር ዲማ ነገዎ በበኩላቸው፥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዚህ በፊት በሚስዮኑ የአንድ ወገን ጥቅም የሚያስከብር ተብሎ የሚወሰድ መሆኑንና አሁን ግን ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በማድረግ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተቋም መሆኑ በማሳየት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ትልቅ እመርታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም ተቋሙ እያደረገ ያለው የለውጥ እና የሪፎርም ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን መገንዘባቸውን የተናገሩ ሲሆን፥ በቀጣይ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የፓርላማ ዲፕሎማሲን ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን መጥቀሳቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.