የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሀገራዊ የለውጥ ሥራውን ስኬታማ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ የለውጥ ሥራው ስኬታማ እንዲሆን በትኩረት እየሰራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዘጠኝ ወር የሥራ አፈጻጸም ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ከክልል የዘርፍ ቢሮዎች ጋር በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ እያካሄደ ነው፡፡
የትራንስፖርትና ጅስቲክስ ሚኒስቴር ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ፥ የትራንስፖርት ዘርፍ ሁሉንም የልማት ሥራዎች የሚነካ ነው ብለዋል።
ሀገራዊ ተግባራትን የተሳካ አድርጎ በቅልጥፍና ማከናወን እንዲቻል ሚኒስቴሩ የበኩሉን አስቻይ ሁኔታ እንደሚፈጥር የገለፁት ሚኒስትሯ፥ የመንገድ ተደራሽነትን ከደህንነት ጋር በማስተሳሰር ለአገልግሎት ቀልጣፋ እንዲሆን አድርጎ መስራት ላይ ትኩረት ይደረጋልም ነው ያሉት።
ለዚህም የተስተካከለ የትራንስፖርት ፍሰትን በመፍጠር የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግና ተደራሽነትን ለማስፋት ሚኒስቴሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ሁሉም ክልሎች ሀገራዊ የዘርፉን ዕቅድ ለማሳካት እንዲሰሩ ያሳሰቡት ሚኒስትሯ የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው ክልሎች ተሞክሮ በማጋራት በዘርፉ የተከናወኑ መልካም ተግባራትን ሁሉም ክልሎች መተግበር ይገባቸዋል ማለታቸውን ከቤንች ሸኮ ዞን ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡