ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና አቶ ደስታ ሌዳሞ ለ81ኛው የኢትዮጵያ ዐርበኞች ድል መታሰቢያ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ለ81ኛው የኢትዮጵያ ዐርበኞች ድል መታሰቢያ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
አርበኝነት ከራስ በላይ ለታላቅ አላማ፣ ለሃገርና ለህዝብ ሰላም እና ደህንነት የመቆም የነፃነትና የሉዓላዊነት ዘውድ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዓሉን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው፥ ለሀገር ሉዓላዊነት ሲሉ ታላቅ መስዋዕትነት ከፍለው ነፃነቷ የተከበረች ሐገር ለትውልድ ያስተላለፉት አባቶቻችን ታላቅ ልዕልናን የተጎናፀፉ የትውልዱ ተምሳሌት ናቸው ሲሉ ለ81ኛው የአርበኞች ቀን መታሰቢያ በዓል ባስተላለፉት መልእክት ገልጸዋል፡፡
ጣሊያን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመዳፈር ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት አርበኞች ኢትዮጵያን አናስደፍርም በማለት በዱር በገደሉ ያደረጉትን ተጋድሎ ታሪክ ይዘክረዋል ብለዋል።
አርበኞች የሀገራቸውን ፍቅር በማስቀደም በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምስራቅና በምዕራብ በመዝመት ጠላት ሐገራችንን በወረረበት ወቅት ዘር፣ ቀለም፣ ኃይማኖትንና ማንነትን ሳይለዩ ተቀናጅተው ጣልያንን አሸንፈው ወደ መጣባት አንዲመለስ አድርገዋል ማለታቸውን ከሲዳማ ክልል ፕሬዚዳን ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡