ታሊባን በአፍጋኒስታን ወታደሮች ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት እንደሚቀጥል ገለጸ
አዲስ አበባ ፣የካቲት 24፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ታሊባን በአፍጋኒስታን የመንግስት ወታደሮች ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ታሊብን በአፍጋኒስታን ዘላቂ ሰላምን ማስፈን የሚያስችል የሰላም ስምምነት ከአንድ ቀን በፊት ከአሜሪካ ጋር መፈራረሙ ይታወቃል።
በስምምነቱም በአፍጋኒስታን እየተስተዋለ ያለውን ቀውስ በዘላቂነት ለመፍታት ታጣቂ ቡድኑ ከሀገሪቱ መንግስት ጋር የሚያደርገው የሰላም ውይይት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተመላክቷል።
ይሁን እንጂ ታሊባን የፈረመውን የሰላም ስምምነት በማፍረስ የአፍጋኒስታን መንግስት ያሰራቸውን 5 ሺህ የታጣቂ ቡድኑ አባላት እስካልፈታ ድረስ ምንም አይነት ውይይት እንደማያካሂድ አስታውቋል።
ከዚህ ባለፈም በአፍጋኒስታን መንግስት ወታደሮች ላይ እየወሰደ ያለውን ጥቃት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የገለጸው።
የአፍጋኒስታን ፕሬዚዳንት አሽራፊ ጋኒ በበኩላቸው ÷ ከታሊባን ጋር እስረኞችን በመፍታት ዙሪያ ምንም አይነት ስምምነት አለመደረጉን ተናግረዋል።
ሀገራቸው እስረኞችን ለመልቀቅ ዝግጁ አለመሆኗን የገለጹት ፕሬዚዳንት አሽራፍ ጋኒ፥ ይህም ለሰላማዊ ድርድር ቅድመ ሁኔታ ሊሆን እንደማይገባ አብራርተዋል።
ምንጭ፥ ቢቢሲ