Fana: At a Speed of Life!

በዱባይና በአጅማን ግዛቶች በሕክምና የቆዩ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሥራ ይሠራል- አምባሳደር አክሊሉ ከበደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዱባይና በአጅማን ግዛቶች ለረጅም ጊዜ በሕክምና ላይ የቆዩ ዜጎች ህክምናቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሥራ እንደሚሰራ አምባሳደር አክሊሉ ከበደ ተናገሩ::
በዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ቆንስል ጄኔራል አምባሳደር አክሊሉ ከበደና ዲፕሎማቶች እንዲሁም ከኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ ማህበር ቦርድ አባላትና ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች የተውጣጣ ቡድን በዱባይ እና በአጅማን ግዛቶች ለረጅም ጊዜ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው የሚገኙ ዜጎችን ጎብኝቷል፡፡
በዱባይ አስቴር ሆስፒታል፣ ሳዑዲ ጀርመን ሆስፒታል እንዲሁም በአጅማን ግዛት በቶምባይ ሆስፒታል ሕክምና ሲደረግላቸው የቆዩ ዜጎች በጉብኝቱ መጠየቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
በወቅቱም አምባሳደር አክሊሉ ከበደ ዜጎቹ እየተደረገላቸው የሚገኘውን የሕክምና ክትትልና አሁን የሚገኙበትን የጤና ሁኔታ እንዲሁም ወደፊት ስለሚኖረው አጠቃላይ ሁኔታ በተመለከተ ከሆስፒታሎቹ የሥራ ኃላፊዎችና የሕክምና ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በቀጣይም ዜጎቹን በተመለከተ ከሆስፒታሎቹ ጋር በመሆን የሚደረገው ክትትልና ድጋፍ እንደሚቀጥልና ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሥራ እንደሚሰራም አመላክተዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.